ቀጥታ፡

ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመወዳደሪያ ምልክት ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመወዳደሪያ ምልክት ይፋ አደረገ።

ቦርዱ የዕጩዎች ስነ ምግባር ደንብ መፈረሚያ መርሐ ግብርም እያካሄደ ሲሆን፤ በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር እና አባላት እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ እያደረገ ያለውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል።

አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎችን ማስመዝገባቸውን ገልጸው፤ የመራጮች ምዝገባ ለማከናወን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

የምርጫ አስፈጻሚዎች የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው፤ የመራጮች ትምህርት ለሚሰጡ 169 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

የምርጫ ቁሳቁስ ዝግጅት ያለበትን ደረጃ ቦርዱ ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ማስጎበኘቱንም ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው የፓርቲዎች የምርጫ ምልክት መራጮች የሚፈልጉትን ፓርቲ ምልክት አውቀው እንዲመርጡ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ፍትሃዊ እንዲሆን የዕጩዎች የሥነ-ምግባር ደንብ የተዘጋጀ መሆኑን አመልክተው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎችም መመሪያውን እንደሚፈርሙ ተናግረዋል።

ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም