ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የአሰራር ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተዳራሽ ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዘርግቷል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት የአሰራር ስርዓቱን ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማሟላት ወደ ተግባር መግባቱን ገለጸ፡፡ 

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ አዲስ እና ወሳኝ የሆነ የፍትህ አካል ነው። 

ይህ ፍርድ ቤት የተቋቋመው በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013 መሰረት ሲሆን መደበኛ ፍርድ ቤቶች ካላቸው የሥራ ጫና እና ከዘርፉ ልዩ ባህሪ አንጻር ጉዳዮችን በብቃት ለመዳኘት እንዲቻል የተቋቋመ ነው። 

ዋና ዓላማው በገበያው ተሳታፊዎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን በገለልተኝነት እና በባለሙያ የሚመረምር ሲሆን ይህ ፍርድ ቤት ገበያው በታማኝነት እንዲመራ ለማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል።  

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን በሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ 

ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የተቋሙን ሰራተኛ ማሟላት ጨምሮ አበረታች ስራ መስራቱን ጠቅሰው ፍርድ ቤቱ የሚመራበት የስነ-ስርዓት መመሪያ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ ዘመናዊና ተደራሽ እንዲሆን ተደርጎ መደራጀቱን የገለጹት ሰብሳቢ ዳኛው፤ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነው ይግባኝ ማቅረብ የሚችሉበት የቴክኖሎጂ ስርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በዚህም ተገልጋዮች የችሎት ሂደቱን በቪዲዮ ኮንፈረንስ መከታተል የሚችሉበት ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመው፤ ችሎቱም የተሟላ የድምፅና የምስል ቀረጻ ቴክኖሎጂ የተሟላለት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ቀጠናዊ ትብብርን ለማጠናከርና አቅምን ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ፍርድ ቤቱ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ከነዚህም ጥረቶች መካከል ከታንዛኒያ አቻ ተቋም ጋር በቅርቡ የመግባቢያ ስምምነት ለመፈረም በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የዳኝነት ተሞክሮ ለማጋራት እና በትብብር ለመስራት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቶች ፎረም ለመመስረት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ይህም ቀጠናዊ የገበያ ትስስርን ለማጠናከር እና ወጥ የሆነ የዳኝነት ስርዓት ለመዘርጋት እንደሚያግዝ ታምኖበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም