7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የትግራይ ክልል ሕዝብ ይበጁኛል የሚላቸውን ወኪሎቹ በነፃነት ለመምረጥ የሚያስችለው ወሳኝ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የትግራይ ክልል ሕዝብ ይበጁኛል የሚላቸውን ወኪሎቹ በነፃነት ለመምረጥ የሚያስችለው ወሳኝ መድረክ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 14/2018 (ኢዜአ)፡- ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የትግራይ ክልል ሕዝብ ይበጁኛል የሚላቸውን ወኪሎቹን በነፃነት ለመምረጥ የሚያስችለው ወሳኝ መድረክ መሆኑን የስምረት ፓርቲ ምክር ቤት አባል ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) ገለጹ።
የትግራይ ሕዝብ ከለውጡ ጋር እንዳይራመድ በተጽዕኖ ውስጥ እንዲቆይ መደረጉ ለዓመታት ዋጋ አስከፍሎታል ሲሉም ሽሻይ አማረ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የክልሉ ሕዝብ የተረጋጋና ሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ መደረጉ መጠነኛ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አመልክተዋል።
በዚህ ዓመት በሚካሔደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ሕዝቡ በነጻነት ወጥቶ መምረጥ እንደሚፈልግ ገልጸው፤ ለዚህም በክልሉ አካታችና አሳታፊ የሆነ ምርጫ ሊካሔድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በልዩ ትኩረት በርብርብ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ዕውቅና የሌለው የሕወሃት ቡድን በትግራይ ክልል ምርጫ እንዳይካሔድ ፍላጎት እንዳለው ጠቁመው፤ ይህ ሁኔታ በሕጋዊ አግባብ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
ምርጫው እንዲከናወን የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ለክልሉ ሕዝብ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም የትግራይ ሕዝብ ለሚያነሳው ጥያቄ ፍትሐዊ ምላሽ እንዲያገኝና ተደማጭ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
ሌላው በኢትዮጵያ በሂደት ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክር የሁሉንም ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ መቋቋሙ በየአካባቢው ለሚከሰቱና አግባብነት ለሌላቸው ልዩነቶች ምላሽ የሚሰጥ ነው ብለዋል።
በተለይም ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ዕድሎችን ይዞ የሚመጣ ትልቅ መፍትሔ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ሀገራዊ የምክክር ሒደቱ አካታችነትን ባረጋገጠ መልኩ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አመልክተው፤ የትግራይ ሕዝብ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ አጀንዳውን ማውጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።