የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞቹን ጥቅም የሚያስከብር ታላቅ ተቋም ነው - አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞቹን ጥቅም የሚያስከብር ታላቅ ተቋም ነው - አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞቹን ጥቅም በዘላቂነት የሚያስከብር ታላቅ ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ 11ኛውን የሕብረት የስምምነት ተፈራርመዋል።
የሕብረት ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ፕሬዝዳንት መገርሳ አስፋው ተፈራርመዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ የሕብረት ስምምነቱ የኢትዮጵያን አየር መንገድ ቀጣይነት ያለው ስኬት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
የተቋማት ጠንካራ የሥራ ማኅበራት የሠራተኞችን ተጠቃሚነት በማስከበር የተቋማት ውጤታማነትን ለማስቀጠል ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የሕብረት ስምምነቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ዕድገት በማፋጠን በስሩ ያሉ ሠራተኞችን ጥቅም በዘላቂነት የሚያስከብር ታላቅ ዓለም አቀፍ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም የአየር መንገዱን ስኬታማ ጉዞ በማስቀጠል ከማኅበሩ ጋር በሕብረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴዔታ ዳንኤል ተሬሳ በበኩላቸው፤ የአሰሪ ተቋማትና ሠራተኛን መልካም ግንኙነት ማጠናከር የሚስችል ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የአሰሪና ሠራተኛ መልካም ግንኙነትም ምርታማነትን በማሻሻል የጋራ ተጠቃሚነት ማስፈኛ መሳሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሰራተኛ ማኅበር የሕብረት ስምምነትም የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ተናግረዋል።
የሕብረት ስምምነቱ ሰነድ ዘመን ተሻጋሪ የትብብር አስተሳሰቦችን የያዘ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ፕሬዚዳንት መገርሳ አስፋው ናቸው።