የዕዙ አኩሪ የጀግንነት ታሪኮች ተጽፈው አያልቁም - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የዕዙ አኩሪ የጀግንነት ታሪኮች ተጽፈው አያልቁም - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
ሐዋሳ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ተጽፈው የማያልቁ በርካታ አኩሪ የጀግንነት ታሪኮች አሉት ሲሉ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው ''የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎቹ'' በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ ዛሬ በሐዋሳ ተመርቋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት፤ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የተፈጸሙ የጀግንነት ጀብዱዎች ተነግረው የማያልቁ ናቸው ብለዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝም በመጽሐፍ ተጽፈው የማያልቁ አኩሪ የጀግንነት ታሪኮች እንዳሉት ጠቅሰው፤ ይህን የጀግንነት ታሪክም ለቀጣዮቹ ጀግኖች በአግባቡ ሠንዶ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የሀገር ዳር ድንበርንና ሉዓላዊነትን ለማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለ፣ ሀገርና ሕዝብ የሚኮሩበት ታሪክ የሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
''የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎቹ'' መጽሐፍ በስድስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን፤ የዕዙ ታሪኮችን በ526 ገጾቹ ያስቃኛል።
በዚህም መሠረት፤ የልዩ ዘመቻዎች ኃይል በኢትዮጵያ፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የአሁን ተጋድሎ ታሪክ፣ ድንበር ያልገደበው የጀግንነት ውሎ፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ቀደምት የተጋድሎ ታሪክ፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝና ሕብረተሰብ እንዲሁም የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የነገ ትልም በሚሉ ርዕሶች በየምዕራፉ ዝርዝር ሐሳቦችን ይዟል።
መጽሐፉ ዕዙ ከተመሰረተበት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ እስከአሁን ያሉትን የ65 ዓመታት የተጋድሎ ታሪክ በፎቶ አስደግፎ መያዙም ተመላክቷል።