የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዓላማ ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን ማጠናከር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዓላማ ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን ማጠናከር ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ዓላማ የዘመናት ሥብራትን ለመጠገንና ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን ማጠናከር ነው።
በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የምትታተመው "ነጋሪ" መጽሔት፤ "ምክክር ለሀገር ክብር" በሚል ርዕስ የሀገራዊ ምክክሩን የዘመናት ሥብራትን ለመጠገን፣ የኮሚሽኑ አራት የክዋኔ ምዕራፎች፣ አካታችነትና ተሳትፎ እንዲሁም ተግዳሮቶችና የቀጣይ የሥራ አቅጣጫዎችን ዳሥሣለች።
በዚህም ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ፖለቲካዊ ችግሮችንና ጫፍ የረገጡ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት እና ለትውልድ የምትመች ሀገር ለመገንባት ሀገራዊ ምክክር መጀመሯ ተብራርቷል።
እንዲሁም የታሪክ አረዳድ ልዩነትን በተመለከተ በሀገር ግንባታ ታሪክ፣ በሰንደቅ ዓላማና በሕገ-መንግሥት ላይ ያሉ አለመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት መታቀዱም ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀገራዊ ምክክሩን በተመለከተ የሰጡትን ማብራሪያ በመጥቀስ፤ ምክክሩ የዘመናት ሥብራትን ለመጠገንና ከተቃርኖ ይልቅ ተዛምዶን ለማጠናከር ማለሙን መግለጻቸውን ነጋሪ አብራርታለች።
መንግሥት ለውጤታማነቱ ቁርጠኛ መሆኑንም ማረጋገጣቸውን ነጋሪ ተመልክታለች።
በዐዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራዎቹን በአራት ዋና ዋና ምዕራፎች ከፋፍሎ እያከናወነ እንደሚገኝም በመጽሔቱ ተመላክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት 80 በመቶ የሚሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑም ተጠቁሟል።
በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ዜጎችም ሐሳባቸው እንዲደመጥ የማረሚያ ቤት ታራሚዎችን የማሳተፍ እንቅስቃሴ መከናወኑ ተመላክቷል።
ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ ችግር ወጥታ የጋራ መግባባትና ዘላቂ ሰላም የምታሰፍንበት "ወርቃማ ዕድል" መሆኑን መጽሔቷ አፅንኦት ሰጥታለች ።