ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የመረጃና የመዝናኛ ይዘቶችን መመልከት የሚያስችላቸውን ቴሌስትሪም የዲጂታል አማራጭ አገልግሎት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የመረጃና የመዝናኛ ይዘቶችን መመልከት የሚያስችላቸውን ቴሌስትሪም የዲጂታል አማራጭ አገልግሎት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የመረጃና የመዝናኛ ይዘቶችን መመልከት የሚያስችላቸውን ቴሌስትሪም (TeleStream) የዲጂታል አማራጭ አገልግሎት ዛሬ ይፋ አደረገ።
በዚህ ወቅት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ቴሌስትሪም በመዝናኛ፣ ትምህርት፣ ጤና እና በተለያዩ ዘርፎች ይዘትን በማዘጋጀትና ለሚሊዮኖች ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ቴሌስትሪም (TeleStream) የዲጂታል አማራጭ አገልግሎቱም ሃሳብ ያላቸው አካላት ይዘት በመፍጠር የሚያስተላልፉበት "ብሔራዊ የዲጂታል ይዘት መድረክ" መሆኑን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ 98 በመቶ መረጃ የሚተላለፈው በሳተላይት መሆኑን በመጥቀስ፤ የዲጂታል መረጃ ተጠቃሚዎች ሁለት በመቶ ብቻ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በዲጂታል አማራጭ የቀረበው የቴሌስትሪም አገልግሎት ምስሎችን በ4k፣ 8k እና በHD ጥራት በማሳየት የሚያድግና የሚሰፋ የቴሌኮም አገልግሎት መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በየጊዜው የሁሉንም ዜጎች የዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የቴክኖሎጂ አማራጮችን እያሰፋ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የቴሌስትሪም (TeleStream) የዲጂታል አማራጭ አገልግሎት ደንበኞችም የአገልግሎት ክፍያዎችን ባሉበት ቦታ በቴሌ ብር መፈጸም እንደሚችሉ አስረድተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም 108 ሚሊዮን ደንበኞችን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ87 ሚሊዮን ደንበኞች 50 ሚለዮን የሚሆኑት የብሮድባንድ ተጠቃሚ በመሆናቸው የቴሌስትሪም አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለሳተላይት ክፍያ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ ያልተቆራረጠ አገልግሎት መስጠት ያስችላል ብለዋል።
የቴሌስትሪም ምርቶችን በዘመን ገበያ በማዘዝ በኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ማዕከላት ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል።