ቀጥታ፡

የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች የመስኖ አውታሮችን በመጠቀም ምርታማነትና ተጠቃሚነታቸውን አሳድገዋል

ሀዋሳ፣ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡-‎በመንግስት የተዘረጉ የመስኖ አውታሮች ዓመቱን ሙሉ በማልማት ምርታማነታቸውን በማሳደግ የተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የወረዳው አርሶ አደሮች መንግስት በአካባቢያቸው የዘረጋላቸውን የመስኖ ልማት አውታር በመጠቀም ገቢያቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በወረዳው የገላልቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሲራቴ ገላ አካባቢያቸው ቆላማ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ በፊት የክረምት ዝናብን ብቻ ጠብቀው በቆሎ ያመርቱ እንደነበር ገልፀዋል፡፡

በዓመት አንዴ የሚያመርቱት የበቆሎ ምርት ከቤት ውስጥ ፍጆታና አነስተኛ ገቢ ከማስገኘት ባለፈ የተሻለ ተጠቃሚ ሳያደርጋቸው መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት መንግስት ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈሩና የመስኖ አውታር በመዘርጋቱ በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት በመቻላቸው በኑሯቸው ላይ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡


 

የጃራ ሂእኔሳ ቀበሌ አርሶ አደር እንዳለ እንግዳ በበኩላቸው አነስተኛ የውሃ ጉድጓድ መሳቢያ ሞተር ተጠቅመው በሚያወጡት ውሃ በዓመት ሦስት ጊዜ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

መስኖ በመጀመሩ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ዓመቱን ሙሉ ማምረት መጀመራቸውን ገልጸው፣ መንግስትም የውሃ መሳቢያ ሞተርን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረጉን ተናግረዋል።

በዓመት ሦስት ጊዜ ጥቅል ጎመንና ሌሎች አትክልቶችን እንደሚያመርቱ ገልፀው በአንድ ዙር እስከ 300 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በክልሉ የመስኖ ልማት ሥራ በአብዛኛው ከወንዞች፣ ጅረቶችና አነስተኛ ጉድጓዶች ውሃ በሞተር በመሳብ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በቆላማና ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ፕሮጀክቶችን የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በነዚህ አካባቢዎች በቅርብ ጊዜያት ብቻ 6ሺህ ሄክታር መሬት የሚያለሙ የተለያዩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዕውን መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሀዋሳ ዙሪያና ሎካ አባያ ያሉ ወረዳዎች ከዚህ በፊት በዓመት አንድ ጊዜ በቆሎ ከማምረት ወጥተው ዓመቱን ሙሉ ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህም አርሶ አደሩን የተሻለ ተጠቃሚ አድርጓል ያሉት ኃላፊው ልማቱ የአካባቢውን ገበያ በማረጋጋትም ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አመልክተዋል።

በዘንድሮው በጋ በመስኖ ለማልማት ከታቀደው 80 ሺህ ሄክታር መሬት እስካሁን ድረስ 73 ሺህ ሄክታሩ መልማቱንም ተናግረዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም