ቀጥታ፡

የቡና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ የቡና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል፡፡


 

በጉባኤው ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሀገሪቱ በዘርፉ የጀመረችው የጥራትና የብዛት ምርት የማሳደግ ባህል ለውጭ ምንዛሬ ግኝት መጠናከር ትልቅ አቅም እየሆነ ነው።

ለዚህም እንደ ማሳያ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የቡና ምርት የሶስት እጥፍ እድገት ማስመዝገቡን ጠቁመዋል።

ቀደም ሲል በሄክታር ስድስት ኩንታል የነበረው የቡና ምርት በአሁኑ ወቅት ወደ አሥር ኩንታልና ከዚያ በላይ ከፍ እንዲል ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የቡና ማህበር ከባለስልጣኑ ጋር በመቀናጀት የዘርፉን ተዋንያን በማሰልጠንና የስራ እንቅስቃሴው በእውቀትና በክህሎት እንዲመራ በማድረግ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በያዝነው በጀት ዓመት ከቡና ሽያጭ ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት የታቀደውን ግብ ለማሳካት ማህበሩ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቡና ንግድ ስርአቱ ይበልጥ እንዲሳለጥ ባለድርሻ አካላት ምርታቸውን በወቅቱ ለገበያ ማቅረብ እንዳለባቸውና ዋጋ ሲተምኑም ዓለም አቀፍ ገበያን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ጉባኤው የኢትዮጵያን አረንጓዴ ወርቅ ይበልጥ ለማዘመንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ማህበሩ ባካሄደው 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንቱ እንደገለጹት፣ ባለፉት ጊዜያት የቡና አመራረት ዘዴን በቴክኖሎጂና በምርምር ለማገዝ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

አርሶ አደሮች የተሻሻሉና ምርታማ የቡና ዝርያዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው፤ በቡናው ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮች አቅራቢዎችና ላኪዎች በንግድ ሂደቱ ውስጥ በቀላሉ የሚገናኙበትና መረጃ የሚለዋወጡበት መድረክ መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡

የቡና ልማት ስራው በዘመናዊ የእርሻ ዘዴዎች እንዲደገፍ በማድረግ ረገድ ማህበሩ ጉልህ ሚና መጫወቱ ጠቅሰዋል፡፡

3ኛ ጠቅላላ ጉባኤው በዋናነት እስካሁን የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም፣ በቀጣይም የቡና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በሚያስችሉ ስልቶች ላይ ለመምከር ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡


 

የማህበሩ አባላት አቶ ፈጠነ የኋላሸት እና አቶ ደግፌ ኢድሉ በበኩላቸው የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ከተለያዩ የምርምር ተቋማት በጋራ በመሆን የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በመትከል ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግን ጨምሮ ለዘርፉ እድገት የሚያደረጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም