አስቻይ ፖሊሲና ህጎችን በመተግበር ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አስቻይ ፖሊሲና ህጎችን በመተግበር ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
ሀዋሳ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- አስቻይ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊስና ህጎችን በመተግበር ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን አስታወቀ።
"ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት፣የሚዲያ አስተዳደርና ቁጥጥር በኢትዮጵያ" በሚል ርእስ ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ውይይት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተካሄዷል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛው ተስፋዬ በወቅቱ እንደገለጹት የሃሳብ ነጻነት በአለም አቀፍ ህጎችና ህገ-መንግስቱ ውስጥ የተካተተ መረጃ የማግኘትና ለሌሎች መብቶች ጥበቃ የሚያደርግ መብት ነው።
በዚህም እንደ ሀገር አስቻይ ፖሊሲዎችና ህጎችን በማውጣትና በመተግበር ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የ2012ቱ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲና እሱን ተከትለው የወጡ አዋጆችና ህጎች ከዚህ ቀደም የነበሩ አሳሪ ህጎችን በመሻር ለሚዲያ አስተዳደርና ቁጥጥር ስርዓቱ ምቹ መደላድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይም ግልጽና ቀላል የፈቃድ አሰጣጥ ስርዓትን በመዘርጋት የሚዲያውን ምህዳር በቁጥርና በዓይነት ማስፋት መቻሉን ጠቅሰው በሀገሪቱ 310 የሚደርሱ መገናኛ ብዙሃን ፈቃድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
የጋራ የቁጥጥር ስርዓትን በመዘርጋትም በርካታ ተቋማትና የሙያ ማህበራትን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የሀሳብ ነጻነትን የሚገድቡ ሀሰተኛ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮች እንዲወገዱ የሚያደርግ አዋጅ በማውጣት ችግሩን የመከላከል ስራ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በውይይቱ የጸደቁ ህጎች ተግባራዊነት፣ በወጡ ዝርዝር ህጎችና በመገናኛ ብዙሃን አገልግሎት አሰጣጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸውን ገልጸዋል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የልማት ጥናትና የጋዜጠኝነት ተባባሪ ፕሮፌሰር መልሰው ደጀኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ ለማንኛውም እድገትና ልማት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሃገር የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲን ተከትለው የወጡ ህጎችና አዋጆችን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ምህዳሩን እንዲያሰፉ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ራሳቸውን በራሳቸው መቆጣጠር የሚያስችላቸውን ተቋማዊ አንድነት በመፍጠር አቅማቸውን ማጎልበትና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን እንዲረጋገጥ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገራዊና ቀጠናዊ ፋይዳ ባላቸውና የፖሊሲ ግብዓት በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ በኃላፊነት መስራት እንዳለባቸው የተናገሩት ደግሞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዘለቀ አርፍጮ (ፕ/ር) ናቸው፡፡
የዛሬው የፖሊሲ ውይይት ለ3ኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ስድስት ተመሳሳይ መድረኮችን በማዘጋጀት የሃሳብ የበላይነትን የማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የማጎልበት ተግባር እንደሚጠናከርም ገልጸዋል።
በመድረኩ ሁለት የመወያያ ሃሳቦች የቀረቡ ሲሆን የጋዜጠኝነትና ስነ-ተግባቦት ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።