ቀጥታ፡

ቅድሚያ ለሴቶች የሩጫ ውድድር በመጋቢት ወር ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- 23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ለሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር መጋቢት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ይደረጋል።

ይህ በየዓመቱ ለሴቶች ብቻ የሚዘጋጀው የ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር መነሻ እና መድረሻው ቦሌ አትላስ ሆቴል መሆኑ ተገልጿል።


 

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ውድድሩን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ በውድድሩ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

23ኛው ዓመት ቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድር ነገ ምዝገባ እንደሚጀመር ገልጸው፤ ለሶስት ሳምንታት እንደሚቆይ አመላክተዋል።

በውድድሩ ላይ 16 ሺህ ሴቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር፤ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ የአየርላንድ ኤምባሲ እና በሌሎች የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብር የተዘጋጀ ነው።

ውድድሩ የተጀመረው በ1996 ዓ.ም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም