የእንስሳት በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል
አዳማ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- የእንስሳት በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች የበለጠ ሊጠናከሩ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የዶሮ፣ የወተት ላሞችና ጥጆች እንዲሁም የዓሣ ሀብት አያያዝ፣ ሥነ-ሕይወት ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮችን ያሳተፈ የውይይት መድረክ በአዳማ ተካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሣ (ዶ/ር) በመደረኩ ላይ እንዳሉት፣የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የእንሰሳት ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።
የእንሰሳት ዝርያዎችን በማሻሻል በምርታማነት ላይ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱንም አንስተዋል።
የእንሰሳት ተዋጽኦ ምርቶች የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሥርዓተ-ምግብን ከማሻሻል አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው አንስተዋል።
ከእንሰሳት ሀብት በዘላቂነት ለመጠቀምና ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ የአንሰሳት ደህንነትና ጤንነት ላይ በበለጠ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ዘመናዊ የእንሰሳት እርባታ በመከተልና ለእንሰሳት ደህነነትና ጤንነት ቅድሚያ በመስጠት ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ መሆን አንደሚገባም አመልክተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤናና ቬተርነሪ ፐብሊክ ሄልዝ መሪ ስራ አስፈፃሚ ሲሳይ ጌታቸው (ዶ/ር) በበኩላቸው በሀገር ደረጃ የእንስሳት በሽታን ቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል የዘርፉን የጤና ሙያተኞችና የኤክስቴሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የእንሰሳት በሽታዎችን ዕውቀት ተኮር በሆነ መልኩ መከላከል እንዲቻል ክትባት መስጠትን ጨምሮ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶክተር ሞክ ያንግ ጋትሏክ እንደገለጹት፣ የእንስሳት ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ የእንስሳት ጤና ኬላዎችና ኪሊኒኮችን በህክምና ቁሳቁስ ከማጠናከር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወኑ ነው።
አርብቶ አደሩ የእንስሳት ሀብት ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ በሽታዎችን አስቀድሞ እንዲከላከል ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።