ቀጥታ፡

"ነጋሪ" መጽሔት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በዝርዝር የዳሰሰ አዲስ ዕትሟን ይዛ ወጥታለች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ "ነጋሪ" መጽሔት ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በዝርዝር የዳሰሰ አዲስ ዕትሟን ይዛ ለንባብ በቅታለች።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ታትማ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን የምትዳስሰው "ነጋሪ" መጽሔት ወቅታዊና ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸው ዐበይት ጉዳዮችን ይዛ ለንባብ በቅታለች።

መጽሔቷ በ8ኛ ዓመት ቁጥር-32 ዕትሟም የባሕር በር እና የታሪክ ምስክርነት፣ ሀገራዊ ምክክር-ለዘላቂ መፍትሔ፣ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት ሩሲያና ሕንድ እንዲሁም የልማትና ኢኮኖሚ ዐበይት ጉዳዮችን ዳሳለች።

ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የነበራት ጥንታዊ የባሕር ላይ ገናናነት እና የታሪክ ዑደትም መጽሔቷ በዐበይት ጉዳይነት ከዳሰሰቻቸው መካከል አንዱ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የንግድና የጦር መርከቦች ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ የነበራቸውን እንቅስቃሴና የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ያውለበለቡበትን የታሪክ ምስክርነት በዝርዝር አቅርባለች።

ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና ጠንካራ የሀገረ መንግስት ግንባታ ለማከናወን እንደ ሁነኛ መፍትሔ የያዘችውን ሀገራዊ የምክክር ሂደት መጽሔቷ በዐቢይ ርዕስነት ተመልክታዋለች።

መጽሔቷ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አስመልክቶ ሁለት ታላላቅ ሀገራትን ትኩረት ሰጥታለች፡፡

ኢትዮጵያና ሩሲያ ከአድዋ ጦርነት ጀምሮ እስከ ዛሬ የዘለቀውንና በተለያዩ የሥርዓተ መንግሥት ለውጦች ያልተናወጠውን የሁለቱን ሀገራት ጥልቅ ወዳጅነት ታስቃኛለች።

የኢትዮጵያና ሕንድ ግንኙነትን በተመለከተም የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ የታየውን "የመኪና እና የቡና ዲፕሎማሲ" እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የፈጠሩትን ጥልቅ ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እንዴት እንደዘገቡት በትንታኔ አቅርባለች።

በተጨማሪም በኢኮኖሚው ዘርፍ መጽሔቷ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የመስኖ ልማት ያስገኛቸው ስኬቶች እና በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ባንኮች መከፈታቸው ለፋይናንስ ዘርፉና ለኢንቨስትመንት እድገት የሚኖራቸው ቁልፍ ጠቀሜታም ዳሳለች።

እንዲሁም "ነጋሪ" መጽሔት በጤና ዙሪያ ያተኮሩ ጠቃሚ ጽሁፎችን በማካተት ሁለገብ መረጃዎችን ለንባብ አብቅታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም