ቀጥታ፡

በወለጋ ዞኖች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋን የሰነቅንባቸው ናቸው

ነቀምት፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- በወለጋ ዞኖች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋን የሰነቅንባቸው ናቸው ሲሉ የነቀምት ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኦሮሚያ ክልል  ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ሰሞኑን በወለጋ ዞኖች የተከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎችን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ጉብኝት ከተካሄደባቸው የልማት ስራዎች መካከልም በማዕድን ዘርፍ የወርቅና የድንጋይ ከሰል ማምረቻዎች፣ በኢንዱስትሪው ረገድ የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎች ይጠቀሳሉ።

ይህንንም አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የነቀምት ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አካባቢያችው መጥተው ጉብኝት በማድረጋቸውና ፕሮጀክቶችን በማስጀመራቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ እንደገለፁት፤ በዞኖቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ትልቅ ተስፋን የሰነቁባቸው ናቸው። 

በነቀምት ከተማ የ04 ቀበሌ ነዋሪ ሼህ ሰዒድ አርጋው ከለውጡ ወዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለወለጋ ዞኖች በሰጡት ትኩረት የልማት ጥያቄዎቻችን በተጨባጭ ምላሽ እያገኙ ነው ብለዋል።

ከልማት ስራዎቹ መካከልም የነቀምቴ ከተማ ኮሪደር ልማት ትልቅ ለውጥ የታየበትና የከተማዋን ገጽታ የቀየረ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ ቀደም አካባቢያቸው የፀጥታ ሁኔታ ስጋት ውስጥ ወድቆ እንደነበር ያነሱት አስተያየት ሰጪው በመንግስት ጥረት ዛሬ ላይ ይህ ሁኔታ ተቀይሮ ማህበረሰቡ ያለ ስጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል።

በአካባቢው ግንባታው የተጀመረው አዲስ የምግብ ማቀነባበሪያ ግዙፍ ፕሮጀክት ለልጆቻችን ሰፊ የስራ እድል ከማመቻቸት ባለፈ  የሀገሪቱን  የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት አጋዥ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልፀዋዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት መደሰታቸውን በመግለፅ በነቀምት ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ስራ ከተማዋ እንድትነቃቃ ማድረጉን የገለፁት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ  ምትኬ ዋሲሁን ናቸው።

በየደረጃው ጠንካራ ስራ በመሰራቱም የጤና፣ የመልካም አስተዳደር፣ የስላምና ፀጥታ እንዲሁም የፍትሕ አገልግሎቶች መሻሻል ማሳየታቸውን አክለዋል።

አቶ በቀለ ወያ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካባቢያችንን ከመጎብኘት ባለፈ የዓመታት ጥያቄያችን የነበረን የግዙፍ ኢንዱስትሪ ግንባታን በማስጀመራቸው ድርብ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም የህዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችን በስፋት ማየት እንዳልተለመደ ገልፀው ዛሬ ላይ ግን ትልቅ ተስፋን የሚሰጡ አዳዲስ የልማት ስራዎችን ማስተዋል ችለናል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቂት ዓመታት በፊት የነቀምቴ ከተማ እና አካባቢውን ነዋሪዎች ባወያዩበት ወቅት በዞኑ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ቃል መግባታቸውን አስታውሰው ዛሬ ላይ ቃላቸውን ጠብቀው ዳግም በመገናኘታችን ተደስቻለሁ ያሉት ደግሞ አቶ ፈዬራ ፉፋ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

ለህዝብ የገባነውን ቃል እንተገብራለን ብለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩም ዝም ብለው ሳይሆን ሰርተው እያሳዩ መሆኑንም አቶ ፈዬራ መስክረዋል።

ግንባታቸው ተጓቶ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ፕሮጀክቶች በጥቂት ዓመታት ተጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን እና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተጀምረው በፍጥነት እየተገነቡ መሆናቸው አስደሳችና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው ብለዋል።

መንግስት ቀን ከሌሊት በመስራት ሀገሩን እየቀየረ ስለመሆኑን በየጊዜው እየታየ ያለ ጉዳይ መሆኑን የገለፁት ነዋሪዎቹ በአካባቢው ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች ስኬት ከመንግስት ጎን በመሆን ያለማሰለስ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም