በምስራቅ ቦረና ዞን በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዷል
ነገሌ ቦረና፣ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡-በምስራቅ ቦረና ዞን በዘንድሮ የበልግ ወቅት በተሻሻለ የግብርና አሰራር ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱንም የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዞኑ ለበልግ አዝመራው እስካሁን ከ37 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡም ተመልክቷል።
ከመጋቢት 15 እስከ ሚያዝያ 30 አካባቢው የበልግ ዝናብ የሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ የእርሻ ስራ የሚጧጧፍበት የአዝመራ ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህ ወቅትም ለሚከናወነው የእርሻ ስራ የዞኑ አርሶ አደሮች የምርታማነት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በመጠቀም የማሳ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ኩልሌ ሸና እንደገለፁት፤ በዞኑ በዘንድሮ የበልግ ወቅት በተሻሻለ የግብርና አሰራር ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዷል።
በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች እስካሁን ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለሁለተኛ ጊዜ ታርሶ ለዘር መዘጋጀቱን ገልፀው የማሳ ዝግጅቱም በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ-ዘዴ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ከበልግ አዝመራው ከ3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ አጠቃላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱንና በማሳ ዝግጅት ምዕራፉ ከ78 ሺህ በላይ ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በጽህፈት ቤቱ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ቡድን መሪ አቶ አብዱረሂም አብዱራህማን በበኩላቸው በዞኑ ለበልግ አዝመራው ከ120 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም 50 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከመሀል አገር ወደ ዞኑ በመጓጓዝ ላይ እንዳለ አሳውቀው ከዚህ ውስጥ 37 ሺህ 600 ኩንታል ወደ ዞኑ ገብቶ ለተለያዩ ወረዳዎች እየተሰራጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግብዓት አቅርቦቱ የተከናወነው በቆላማ ወረዳዎች ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ታሳቢ በማድረግ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዞኑ ሊበን ወረዳ የሜኤሳ ዳሎሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ እስማኤል ማሊማ ሁለት ሄክታር መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ ለዘር ያዘጋጁ ሲሆን በመኸር አዝመራ ያጡትን ምርት የማካካስ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ በበልግ ወቅት አዳዲስ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ የምርት ማሳደጊያዎችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለመጨመር ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።
ለበልግ አዝመራው 8 ሄክታር መሬትን በኩታ ገጠም የእርሻ ስነዘዴ ደጋግመው በማረስ ለዘር ማዘጋጀታቸውን የገለፁት ደግሞ በሊበን ወረዳ የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ወርቁ አለባቸው ናቸው።
ምርትና ምርታማነታቸውን ለማሳደግም ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲቀርብላቸው ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቅርበው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡