በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ199 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለምቷል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ199 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለምቷል
ጊምቢ፣ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ):-በምዕራብ ወለጋ ዞን ከ199 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርና ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በኢኒሼቲቭ እየተከናወኑ ያሉ የግብርና ሥራዎች ውጤታማነታቸው እየተረጋገጠ ነው፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ፈይሳ ሀሜቢሳ በዞኑ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናው ዘርፍ የተጠናከረ ሥራ እየተሰራ ነው።
በተለይም አርሶ አደሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተሰማርቶ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን አንስተው የመስኖ ልማቱን ዓመቱን ሙሉ በማልማት የአርሶ አደሩን የሥራ ባህል ማሻሻሉንም ተናግረዋል።
ዘንድሮ በዞኑ ከ199ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ መልማቱን የገለጹት አቶ ፈይሳ፣ ከለማው መሬትም 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
በበጋ ስንዴ ልማቱ 119ሺህ 604 አርሶ አደሮች በንቃት መሳተፋቸውን ጠቅሰው፣ ለውጤታማነቱ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ለአርሶ አደሩ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዞኑ በልማቱ ከተሳተፉ የላሎ አሳቢ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ሀብታሙ መርጋ እንዳሉት፣ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ ላለሙት ስንዴ ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረጋቸው ሰብሉ በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል።
በመንግስት በኩል በወቅቱ ግብዓት መቅረቡን ገልጸው፣ በባለሙያ ድጋፍ ታግዘው ካለሙት የስንዴ ሰብል የተሻለ ምርት እጠብቃለሁ ብለዋል።
በበጋ ወቅት ካለሙት የስንዴ ሰብል 20 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ ተሰፋ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ከቤት ፍጆታ ያለፈውን ለገበያ ለማቅረብ ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በበጋ ወቅት ስንዴን ማምረት ከጀመሩ ወዲህ በቡና ላይ ብቻ ጥገኛ የነበረው የገቢ ምንጫቸው እያደገ መምጣቱን የተናገሩት ደግሞ አርሶ አደር ልጂቱ ኩመራ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ የግብርና ግብአቶችን ተጠቅመው በበጋ ያለሙትን የስንዴ ሰብል እየተንከባከቡ መሆኑን ተናግረዋል።