ቀጥታ፡

ሀዋሳ ከተማን የቱሪስቶች ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ያለው ስራ ውጤታማ ነው - ከንቲባ ጥራቱ በየነ

ሀዋሳ፤ የካቲት 13/2018 (ኢዜአ)፡- ሀዋሳ ከተማን የቱሪዝም፣ የስፖርትና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጥራቱ በየነ ገለጹ።

ባለፉት ስድስት ወራት ከተማዋን ከጎበኙ ቱሪስቶች አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የከተማዋ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጥራቱ በየነ እንደገለጹት ከተማዋን የቱሪዝም፣ የስፖርት እና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ስኬታማ ናቸው።

በተለያዩ ጊዜያት የሚከናወኑ ባህላዊ፣ መንፈሳዊና ስፖርታዊ ስነ-ስርዓቶች ላይ ለመታደም በርካቶች ወደ ከተማዋ እንደሚመጡ ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በግንባታ ላይ ያሉ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ሲጠናቀቁ በተሻለ መንገድ ተጠቃሚነትን እንደሚያሳድጉ ነው የጠቀሱት።

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ መቅደስ ሁሪሶ በበኩላቸው፤ ከተማዋን ለቱሪስት ምቹ ለማድረግ የተሰሩት ስራዎች የጎብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየሳደገ ነው፡፡ 


 

የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ካደረጉት ምክንያት መካከል በአካባቢው ካለው የተፈጥሮ ሀብት በተጨማሪ በመንግስትና በግል ባለሀብቱ እየተከናወኑ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም 232 ሺህ የሀገር ውስጥ 33 ሺህ 270 ደግሞ የውጪ ጎብኚዎች በሀዋሳ ከተማ ጉብኝት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት።

በዚሁ ወቅትም አካባቢውን ከጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ጉብኚዎች አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ጠቁመዋል።


 

ሀዋሳ ከተማን ሲጎበኙ ያገኘናቸው ሰላማዊት ጌታቸው እንዳሉት፤ እየተካሄዱ ያሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ልማት በውጭ ሀገራት እናያቸው ከነበሩ መስህቦች  የማይተናነሱ ናቸው።

“ቀደም ሲል ለመዝናናት ስንፈልግ ሆቴል ሄደን ነበር አሁን ግን በየመንገዱ መዝናናት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይህ ደግሞ በርካቶችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ነው” ብለዋል።


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መዘምር ዘርፉ በበኩላቸው፤ በየአካባቢው የመስህብ ስፍራዎች እየተገነቡ ይገኛል ይህ ደግሞ ለሀገር እድገት በርካታ እድሎችን ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል።

የመዳረሻ ልማት ስራዎቹ ለርካቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የስራ ባህላችንን ለመቀየር አስችሏል  ነው ያሉት።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም