ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ልማት የታዳሽ ኃይል ብዝኅነትን በማስፋት የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ወሳኝ እርምጃ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ልማት የታዳሽ ኃይል ብዝኅነትን በማስፋት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥን ወሳኝ የልማት እርምጃ መሆኑን ዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ወቅት የ30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ይታወሳል።

ከብሔራዊ ፕሮጀክቶቹ መካከል ሰላማዊ የኒውክሊየር ልማት መርሃ ግብር፣ የዩሪያ ማዳበሪያ፣ ግዙፍ የአየር ማረፊያ፣ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤቶችና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ይገኙበታል።

ኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ልማት መርሃ ግብር የምታካሂደው ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ጥቅም ላይ እንደሚውል መንግስት ማሳወቁ ይታወሳል።

ይህ መርሃ ግብር የሀገሪቷ የኃይል አቅርቦት ፍላጎትን በማሟላት ፈጣን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገቷን ለማሳለጥ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑ ይገለጻል።

በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ የቴክኒክ ትብብር መምሪያ የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጋሻው ገበየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኒውክሊየር ኃይል ከታዳሽ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ ግብር ለመጠቀም የሚያስፈልጉ የፖሊሲና የመሠረተ ልማት እርምጃዎችን እየወሰደች እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ ግብርም ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያስቀጥል የታዳሽ ኃይል አማራጭ ብዝኅነትን ማስፋት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ድርጅት የኢትዮጵያን ሰላማዊ የኒውክሊየር ኃይል መርሃ ግብር የመጠቀም ጥረት ለማገዝ በአጋርነት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም ለኢትዮጵያ የኒውክሊየር  ኃይል መርሃ ግብር ፕሮጀክት ስኬታማነት የሚያስፈልጉ ሙያዊና የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የኒውክሊየር ኃይል አነስተኛና ነፃ የካርበን ልቀት የኃይል አማራጭ በመሆኑ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የማይበገር አረንጓዴ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

በሌላ መልኩም አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት አማራጭ በመገንባት የኢኮኖሚ ዕድገትን ማሳለጥ የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም