የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ የሚያስፈልገው ነው
ሀዋሳ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ እንደሚያስፈልገው በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ስምምነቶችን መሰረት ያደረገ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባሕር በሯን ማግኘት ደግሞ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም እንዲሁ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙት መምህር ንጉስ በላይ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በታሪክ ኢትዮጵያን ከባህር በር ነጥሎ ማየት የማይታሰብ ነው።
ኢትዮጵያ እድገቷን በማይፈልጉ አካላት የባሕር በር እንዳይኖራት መደረጉ በሌሎች ሀገራት ጥገኛ እንድትሆን ከማድረጉ ባለፈ ዘርፈ ብዙ የእድገት ማነቆዎችን እንድታስተናግድ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የባሕር በር ጥያቄ ከታሪክ፣ ከመልክዓ ምድርና ከህግ አንጻር ተገቢ ነው የሚሉት ምሁሩ ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም አቀፍ ሁኔታ ከባህር በር ተነጥሎ መኖር አዳጋች እንደሆነ ገልጸዋል።
እያደገ ከመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚና የህዝቦቿ ቁጥር አንጻር የባህር በር ጥያቄው ፈጣን ምላሽ የሚያስፈለገው ነው ሲሉም አመላክተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ሳይንስ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ምስራቅ ታምሬ(ዶ/ር)፤ በቀጣናው ሀገራት ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያን ከባህር በር ነጥሎ ማየት እንደማይቻል ነው የተናገሩት።
ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያን እድገት በማይፈልጉ አካላት የባሕር በሯን በሴራ ማጣቷ ተገቢነት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር የአሁኑ ትውልድም ቁጭት እንዲፈጥርበት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ከነበራት ታሪክና ከአለም አቀፍ ሕግ አንፃር ጥያቄው ትክክል መሆኑን አመልክተው የባህር በሯን መልሳ ለማግኝት የምታደርገው ጥረት አሁን ካላት የኢኮኖሚ እድገትና የሕዝብ ብዛት አንፃር ተገቢና የህልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
አዲሱ ትውልድ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መብቷን ያጣችበት መንገድ ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን እንዲረዳ በተሻለ መንገድ ግንዛቤ በመፍጠር ምላሽ የሚያገኝበት መንገድ ላይ በትብብር መስራት እንደሚያስፈለግም አመልክተዋል።
በተለይም የውስጥ አንድነትን፣ ሰላምንና አብሮነትን በማጠናከር ባጠረ ጊዜ የባህር በር ጥያቄው ምላሽ አንዲያገኝ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።