ቀጥታ፡

ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የአርብቶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል ያግዛሉ

ነገሌ ቦረና፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ቦረና ዞን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የአርብቶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል እንደሚያግዙ ተመላከተ፡፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች በመፋጠን ላይ መሆናቸውን የዞኑ ገንዘብ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የምስራቅ ቦረና ዞን ገንዘብ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዶዮ ቦርቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በምስራቅ ቦረና ዞን መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ሥራ እየተሰራ ነው።



 

በዚህ ዓመት በዞኑ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ 215 የልማት ፕሮጀክቶች ዘጠኝ ወረዳዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፣ ከእነዚህ ውስጥ 183ቱ ዘንድሮ የአዲስ የተጀመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

እንደሀላፊው ገለጻ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ከ800 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ።

በግንባታ ላይ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖ፣ የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድና የድልድይ መሰረተ ልማቶች እንደሚጠቀሱ ገልጸው፣ እስካሁን የ87 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ሥራ መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የሁለት ድልድዮች፣ አምስት ትምህርት ቤቶችና የሁለት የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጠናቀቁን ነው የገለጹት።፡

ቀሪዎቹ የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ከ54 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸው ሁሉንም የልማት ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡


 

የፕሮጀክቶቹ መገንባት የአርብቶ አደሩን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል ረገድ ጠቀሜታቸው የጎላ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በተለይም የድልድይና የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ቀበሌን ከቀበሌና ምስራቅ ቦረና ዞንን ከተጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር የሚያገናኙ  ናቸው ብለዋል፡፡

በዞኑ አሬሮ ወረዳ የፉልዱዋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዲቃ ሁቃ፤ ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ መንግስት እያሳያ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያደንቁ ገልጸዋል፡፡

የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማቃለል ለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም