ቀጥታ፡

በክልሉ የተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ተኪና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እንዲያመርቱ ዕድል ፈጥሯል

ባህር ዳር ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል የተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንዱስትሪዎች ተኪና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እንዲያመርቱ ዕድል መፍጠሩን  የዘርፉ የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ።

የመደመር መንግስት አምስት የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ዘርፎች አንዱ አምራች ኢንዱስትሪ ነው።

ከለውጡ በፊት በአሰራር ማነቆዎች ምክንያት በርካታ ኢንዱስትሪዎች ማምረት አቁመው እንደነበር የዘርፉ የሥራ ሃላፊዎች ይናገራሉ።

ይህም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ምርቶች እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ የዘርፉን እንቅስቃሴ ማዳከሙን አስታውሰዋል።

የለውጡ መንግስት ከወሰዳቸው እርምጃዎች የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አንዱ ሲሆን በንቅናቄው የዘርፉን ማነቆዎች ለይቶ ከመሰረቱ መፍታት የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ ተደርገዋል።

በዚህም ማምረት አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ከማድረግ ባለፈ የማምረት አቅማቸው መጨመሩን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሥራ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ግርማይ ልጃለም፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቀዛቅዞ የነበረውን ኢንዱስትሪ አነቃቅቷል ብለዋል። 


 

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ያጋጥማቸው የነበሩ የአሰራር ማነቆዎችን በቅንጅት በመፍታት የማምረት አቅማቸውን ማሳደጉንም ገልጸዋል።

ለዘርፉ ከፍተኛ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ በከተማው ባለፉት ስድስት ወራት 50 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 142 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውንና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አመልክተዋል።

የባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ብርሃን ንጉሴ፤ ንቅናቄው ኢንዱስትሪዎች ተኪና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ጥራት ያላቸው ምርቶችን  በብዛት እንዲያመርቱ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።


 

በዘርፉ እየተደረገ ባለው ማበረታቻ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፉ መቀላቀላቸውን አመልክተዋል።

በከተማዋ በዘርፉ በተደረገው ክትትል 77 ኢንዱስትሪዎች ስትራቴጂካል ተኪ ምርቶችን እያመረቱ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ካመረቱት ተኪ ምርትም 66 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሥራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረጉን የገለጹት ደግሞ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ መሃመድ ይማም ናቸው።


 

የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርት በማምረት፣ የኑሮ ወድነትን በማረጋጋትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ሃላፊ ተፈሪ ታረቀኝ፤  የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሻገር ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል።


 

በክልሉ በ2014 ዓ.ም የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 46 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ ከ62 በመቶ በላይ መድረሱ የነቅናቄው ውጤት ነው ብለዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት 85 ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ወደ ምርት እንዲገቡ መደረጉንና ምርት አቁመው የነበሩ 35 ኢንዱስትሪዎችም ሥራ እንዲጀምሩ መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም