ቀጥታ፡

ለመራጮች ምዝገባ የሚያገለግሉ የቁሳቁስ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን የማዘጋጀት ሥራዎችን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስጎብኝቷል።  

በጉብኝቱ ወቅት የቦርዱ የሎጂስቲክስ ኃላፊ አቶ መላኬ አሉላ እንደገለጹት፤ ቁሳቁሶችን ለየምርጫ ጣቢያዎቹ የመለየትና የመደልደል ሥራዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

የዝግጅት ሥራው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 52 ሺህ 720 የምርጫ ጣቢያዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ለእያንዳንዱ ጣቢያ ተደራሽ የሚደረጉ የጽሕፈት መሣሪያዎች፣ የቅሬታ አፈታት መመሪያዎች እና መረጃ ሰጭ ፖስተሮች በዝርዝር ተለይተው እየተዘጋጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በሂደቱ ላይ የጥራት ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የምርጫ ቁሳቁሶቹ በወረቀትና በሰው ኃይል ለሚከናወነው ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የምዝገባ ሂደት ለማከናወን የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም