ኢትዮጵያ በቱሪዝም ልማት ዘርፍ እያከናወነች የምትገኘው ድንቅ ተግባር ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ልማት ዘርፍ እያከናወነች የምትገኘው ድንቅ ተግባር ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ልማት ዘርፍ እያከናወነች የምትገኘው ድንቅ ተግባር ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆንና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የፓን አፍሪካ ቱሪዝም ቦርድ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ማርያም ሌሲያን ገለጹ።
አምባሳደር ማርያም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ጸጋዎች በማድነቅ ኢትዮጵያ የሁላችንም ምድርና ቀደምት ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ባህልና ማንነታቸውን በመጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ መቻላቸው እጅግ የሚያስደንቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የሚታዩ ውብ የባህል አልባሳት፣ ልዩ የቡና መዓዛና ሀገር በቀል ሙዚቃዎች ሀገሪቱ የራሷን ማንነት ጠብቃ እንድትቆይ ያደረገችው ጥረትና ሌሎችም ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የሀገሪቱን የቱሪዝም እድገት ከሚያፋጥኑ መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጥንካሬ በዋናነት አንስተዋል።
አየር መንገዱ ያለው ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት ቱሪስቶች ያለምንም እንግልት ወደ ሀገሪቱ እንዲመጡና እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ንፁህ፣ ሰላማዊና የሕዝቧ እንግዳ ተቀባይነት የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቷ ይህ መልካም ባህሪ ቱሪስቶችን አንዴ መጥተው ሳይወሰኑ ደጋግመው እንዲመጡ የሚያደርግ መሆኑንም ገልጸዋል።
አህጉሪቱ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለመጠቀም ትብብርና ድንበር የለሽ ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የአፍሪካ መሪዎች ለአፍሪካውያን የቪዛ ገደብን እንዲያነሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በአህጉሪቱ ሀገራት መካከል የባቡርና የፈጣን ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ግንባታ ሊፋጠን እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።
በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለዓለም አቀፍ ቱሪዝም መሳካት መሰረት መሆኑንና አፍሪካ በዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ ያላትን ድርሻ ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት በርካታ ተሞክሮዎችን መውሰድ እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል፡፡