ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቡና ምርቷን ለጣሊያን ገበያ በስፋት በማስተዋወቅ የገበያ ድርሻዋን ለማሳደግ እየሠራች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የቡና ምርቷን ለጣሊያን ገበያ በስፋት ለማስተዋወቅና የገበያ ድርሻዋን ለማሳደግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ ገለጹ።    

የኢትዮ-ጣሊያን የቡና ንግድ መድረክ በጣሊያን ሚላን ከተማ ተካሂዷል፡፡    


 

መድረኩን በሮም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር፣ ኮንፊንዱስትሪያ አሳፍሪካና ሜዲትራኒያኖ እንዲሁም ቦኔሊ ኤሬዴ የተባሉ ተቋማት በትብብር ማሰናዳታቸው ተጠቅሷል፡፡

በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሃምቢሳ እንደገለጹት፣ በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከቡና የውጭ ንግድ ከፍተኛ ምንዛሪ ለማግኘት እየሠራች ነው።

ኢትዮጵያ ባሳለፍነው ዓመት ከቡና ኤክስፖርት 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን ጠቅሰው፥ ጥራት ያለውና በጥራቱና በጣዕሙ ተወዳጅ የሆነ የቡና ምርቷን በስፋት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነች መሆኗን አንስተዋል።

ቡና በጣሊያን ማቴይ ዕቅድ በተያዙ ፕሮጀክቶች አማካይነት የሁለቱ ሀገራት ትብብር ያለበት አንዱ መስክ መሆኑን አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የአካባቢ ጥበቃን ለማጎልበት በአረንጓዴ አሻራ ሰፊ ሥራ መሥራቷን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ፤ የጣሊያንን ገበያ በተሻለ ሁኔታ በመረዳት የቡና የገበያ ድርሻን ለማሳደግ አዲስ ስትራቴጂ መነደፉን ተናግረዋል፡፡ 

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ስቴፋኖ ዴ ሊዮ በበኩላቸው፤ ቡና ለሁለቱም ሀገራት ስትራቴጂካዊ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዳዲስ ወጣቶችን ወደ ዘርፉ ለመሳብ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ተደራሽነትን ማሻሻል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ የክብር ቆንስል እና የቦኔሊ ኤሬዴ አጋር ጂያንፒዬሮ ሱቺ፤ የኢትዮ-ጣሊያን የቡና ንግድ መድረክ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግር ጠቅሰዋል፡፡ 

የኮንፊንዱስትሪያ አሳፍሪካ የቦርድ አባል ማሲሚሊዮን ፋቢያን በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እጅግ አስደሳችና ባለ ልዩ ጣዕም የቡና ዝርያ ያላት ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ይህ የንግድ መድረክ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግርና በሚቀጥሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ቡና በጣሊያን ያለውን ድርሻ ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም