ቀጥታ፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዲጂታል ሉዓላዊነትን በተሟላ መልኩ የሚያረጋግጥ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሚያፋጥንና ዲጂታል ሉዓላዊነትን በተሟላ መልኩ የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ተወካይና በኢትዮጵያ የክፍለ አህጉር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፈን ባይኖስ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጅ መጠናቀቁን ተከትሎ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ልዩ ተወካይና በኢትዮጵያ የክፍለ አህጉር ቢሮ ዳይሬክተር ስቴፈን ባይኖስ፤ ዲጂታላይዜሽን የእድገት አቀጣጣይ መሣሪያ ነው ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በልጽገው የምናያቸው የዓለም ሀገራት የደረሱበት የእድገት ደረጃ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በሰጡት ትኩረት ልክ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ለማሳደግ እና ዘመናዊ አሠራሮችን ለመተግበር ያስቀመጠችው አቅጣጫ ይበል የሚያሰኝ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ተከትሎ  የሚታዩ እና ትርጉም ያላቸው ሁለንተናዊ ለውጦች መመዝገባቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሚያፋጥንና ዲጂታል ሉዓላዊነትን በተሟላ መልኩ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ በምታከናውነው ተግባር አብረው እየሰሩ እንደሚገኝ ጠቁመው፤  በቀጣይም ትብብሩን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም