ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ። 

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚጠበቅባቸውም ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው ይፋዊ መርሃ-ግብር ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን የመራጮች ምዝገባም የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ይጀመራል።

ምርጫ የዲሞክራሲ ስርዓትን ይበልጥ ለማጠናከርና ዜጎች ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚያገለግሉትን መሪዎች የሚመርጡበት ነው።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ውሳኔ ሰጪነት በሚጠይቁ አበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በቀጥታ ማሳተፍ ይገባል።

አካል ጉዳተኞች ህገ-መንግስቱ የሰጣቸውን መብቶች ከሚያረጋግጡባቸው ሁነቶች መካከል አንዱ ምርጫ መሆኑንም አንስተዋል።

ቀደም ባሉት ምርጫዎች የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኛው ምቹ ያለመሆን፣ የግንዛቤ እጥረትና በታዛቢነት የመሳተፍ ዕድል አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል። 

ፌዴሬሽኑ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የህግ ማዕቀፎች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የማረጋገጥ ስራ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ማከናወኑን ጠቅሰው፤ አካል ጉዳተኞች በምርጫ ታዛቢነት እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።   

በምርጫው የሚተገበሩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አካል ጉዳተኞችን ከግምት ያስገቡ እንዲሆኑና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ከምርጫ ቦርድ ጋር በትብብር እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል። 

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች በመራጭነትና ዕጩ ተመራጭነት ብሎም በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፓርቲያቸውን የፖለቲካ ፕሮግራም እና ማኒፌስቶ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽና ግልጽ በሆነ መንገድ የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም