ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል- የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች 

ቀብሪደሃር/ጎዴ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፡- 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ በሶማሌ ክልል የቀብሪደሃርና ጎዴ ከተማ የሚኖሩ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ተናገሩ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች እንዳሉት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ይወጣሉ።

በቀብሪደሃር ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ሁሴን መሀመድ፤ ምርጫው ነፃና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የላቀ ድርሻና ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።


 

በዚህም ህዝቡ በምርጫው እንዲሳተፍ የማድረግ ስራ ከሁሉም አካላት ጋር በመቀናጀት እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ሁሉም ዜጋ በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ምርጫው የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ማረጋገጫ ነው ያሉት ደግሞ  የሀገር ሽማግሌ አቶ አብዱላሂ ዑመር ናቸው።


 

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ምርጫው በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲከናወን በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።

የጎዴ ከተማ ነዋሪ ወጣት ከድር ኢብራሂም በበኩሉ፣ ምርጫው ነፃና ሰላማዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀቱንም ተናግሯል።


 

ወጣቶች በጠቅላላ ምርጫው በመሳተፍ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የማንቃት ሥራ እየሰሩ መሆኑን የገለፀው ደግሞ ወጣት በሺር ኦዶዋ ነው።


 

በተለይ ምርጫው ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ሙሉ ዝግጅት ማድረጋቸውንም አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም