ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዓይነተኛ ሚና አለው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዓይነተኛ ሚና አለው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዓይነተኛ ሚና እንዳለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።
ምክክሩ የውስጥ አቅምን በማጠናከር ለሀገራዊ እድገት መፋጠን ተጨማሪ አቅም እንደሚሆንም ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ የማያግባቡ ጉዳዮችን በመለየት በዘላቂነት ለመፍታት ቁልፍ ሚና አለው።
የሀገራትን ልምድና ተሞክሮ በመቅሰም፣ ባህላዊና ትውፊታዊ የምክክር እሴቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል እንዲሁም አጀንዳ በማሰባሰብ ሒደት አካታች የሆነ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረጉ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
ምክክሩ የሀገር ጉዳይ የጋራ ጉዳይ መሆኑን በሁሉም ዜጎች ዘንድ ማስረጽ ከማስቻሉ ባሻገር ልዩነትን አሉታዊ በሆኑ አካሄዶች የመፍታት ባህል እንዲከስም ያደርጋል ነው ያሉት።
በሀገራዊ ምክክር ሒደት ከሚገኙ ጥቅሞች መካከል ልዩነትን ሲፈጥሩ የቆዩ አጀንዳዎች ወደ አንድ የሚመጡበትና የጋራ አቋም መፍጠር የሚቻልበት እድል አንዱና ዋነኛው መሆኑንም አስረድተዋል።
እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ ሀገራዊ ምክክሩ በልማት፣ በእድገት፣ በዲሞክራሲ፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ በደህንነት፣ በሰላምና በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች የጋራ ስሜትና ፍላጎት እንዲኖራቸው መሰረት የሚጥል ነው።
ይህም በዜጎች መካከል ትልቅ ብሔራዊ ጉልበትን በመፍጠር ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ የውስጥ አቅምን በማጠናከር በኩል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ይህም በሁሉም ዘርፎች ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ከፍ ያለ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በተለይም በሀገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና እድገት ላይ ዜጎች የሚያደርጉት ተሳትፎ እንዲጠናከር እድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
በፖለቲካና ዲፕሎማሲ ዘርፎች የሚከናወኑ ተግባራት እንዲሁ በጋራ ትብብርና በአንድነት መንፈስ እንዲከናወኑ ሀገራዊ ምክክሩ አስቻይ ሁኔታን በመፍጠር የተጀመረውን ሀገራዊ እድገት ለማፋጠን ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል፡፡