ቀጥታ፡

በብሄረሰብ አስተዳደሩ ሰላምን በማጽናትና የልማት ሥራዎችን በማፋጠን ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል 

ሰቆጣ ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰላምን በማጽናትና የልማት ሥራዎችን በማፋጠን  ውጤታማ ተግባራትን ማከናወን መቻሉ ተገለጸ።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ በሰቆጣ ከተማ ተካሂዷል።


 

የአስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ ሹመት ጥላሁን እንደገለፁት፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተካሄደው የሰላም ግንባታና የልማት ስራ ውጤት አስገኝቷል።

ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ቴክኖሎጂና ግብዓት በመጠቀም በመኸር ምርት ዘመን ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

በበጋ መስኖ ልማት ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብዓትና የውሃ መሳቢያ ሞተር  በማቅረብ ከራሱ አልፎ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እንዲያመርት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሕብረተሰቡን የማሕበራዊና ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት በተደረገ ጥረትም ውጤት መምጣቱን አንስተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የ142 ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ጠቁመው፣ ቀሪዎቹን በተቀመጠላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው ብለዋል።


 

የሰቆጣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እሚያምረው ጌጤ፤በወረዳው የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመስኖና የእንስሳት ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ገልጸዋል።

ሕብረተሰቡ ቅሬታ ያነሳባቸው የነበሩ የማህበራዊ አገልግሎቶች መሰረተ ልማትን ለማሟላት ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር ሰፊ ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።


 

የጋዝጊብላ ወረዳ አስተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ባለፉት 6 ወራት በሕብረተሰቡና በጸጥታ ሃይሉ ትብብር ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስጠበቅ መቻሉን ተናግረዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራን በነቃ የህዝብ ተሳትፎ ማሳካት መቻሉን ጠቁመው፣ በቀጣይም የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የሰላምና የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም