ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ አስደናቂ የልማት ስኬቶች የመዲናዋን የአፍሪካ ሕብረት ማዕከልነት በተግባር የገለጡ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስደናቂ የልማት ስኬቶች የመዲናዋን የአፍሪካ ሕብረት ማዕከልነት በተግባር የገለጡ መሆናቸውን የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊ ልዑካን ገለጹ።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ''ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የታደሙ ሀገራት ልዑካን ቡድን አባላት፤ በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ጥራትና ደረጃቸውን የጠበቁ አስደናቂ የልማት ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ማራኪ ገጽታም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚመጥኑና ለአፍሪካ ሀገራት የከተማ ልማት ተነሳሽነትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የዑጋንዳ ልዑክ ኢማኑዌል ካቱምባ፤ የአዲስ አበባ ማራኪ የልማት ውጤቶች ኢትዮጵያ ስኬታማ የዕድገት ጎዳና ላይ መሆኗን የሚያመላክት ነው ብለዋል።


 

ከአምስት ዓመታት በፊት በሚያውቋት አዲስ አበባ የተገነቡ  የንግድ፣ የሆቴል፣ ቱሪዝምና የተለያዩ መሠረተ ልማቶች መዲናዋን ውብ ገጽታ ያላበሱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስኬታማ የለውጥ ምዕራፍም ለዑጋንዳና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በልምድና ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የናሚቢያ ልዑክ ሳይማ ሻኒካ በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ ፈጣን የለውጥ ምዕራፍ በምሳሌነት የሚወሰድ አኩሪ የልማት ስኬት ነው ብለዋል።


 

የአዲስ አበባ የአረንጓዴ ልማት፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና የመሰረተ ልማት ውጤቶች የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት የገለጡና የመንግስትን የአመራር ቁርጠኝነት ያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የታንዛኒያ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ልዑክ ኢንጂነር ላይትነስ ሳሌማ፤ የኢትዮጵያ የከተሜነት ሽግግር በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከተሞችም ሊደገም የሚገባ ተግባር ነው ብለዋል።


 

የህዝቡ ትህትና እና ለእንግዶች ያለው አክብሮት ለከተማዋ ውበት ተጨማሪ ድምቀት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም