ባለፉት ስድስት ወራት ከ18ሺህ ለሚልቁ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ስድስት ወራት ከ18ሺህ ለሚልቁ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል
ደሴ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፡- በተያዘው በጀት ዓመት ያለፉት ስድስት ወራት ከ18ሺህ ለሚልቁ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ መሰረተ ልማት ከማሟላት ባለፈ የሚያሰራ የህግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ለባለሃብቶች ምቹ ከባቢን ፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ተመራጭ መዳረሻ ናት ብለዋል።
የመደመር መንግሥት በዘርፉ መነቃቃትን ለመፍጠርና አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የአሰራር ማሻሻያና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች እየተገበረ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በፌዴራል ደረጃ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ዶላር በላይ በክልሎች ደግሞ ከ610 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ከ18ሺህ በላይ የሀገር ወስጥና የውጭ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አመልክተዋል።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው 17ሺህ 870 ባለሃብቶች በክልሎች እንዲሁም 245ቱ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚሰማሩ ናቸው ብለዋል።
ባለሃብቶቹ በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ከ192ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ፣ የተቀናጀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥና በዘርፉ እየታየ ላለው ውጤት መነሻ መሆኑንም አስረድተዋል።
በቅርቡ ''ኢንቨስት ኢን ኢትዮጵያ'' በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው መርሃ-ግብር ከአንድ ሺህ በላይ አዳዲስ ባለሃብቶችን በመሳብ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የኢንቨስትመንት ሀብቶችን በአግባቡ ለማስተዋወቅና ዘርፉን ለማነቃቃት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 183 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ አንድ ሺህ 867 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አባስ መሀመድ(ዶ/ር) በክልሉ መሰረተ ልማት በማሟላትና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ከ10 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።
የከተማዋ ፈጣን ዕድገትና ልማት ለኢንቨስትመንት ተመራጭ መዳረሻ አድርጓታል ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አይሻ መሀመድ ናቸው።
በአዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ወራት 11 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ከ2ሺህ 500 በላይ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን በመግለጽ።