ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ ትርክትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ ትርክትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው
መቱ፤ የካቲት 13/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ገዢ ትርክትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት ዓይነተኛ መሣሪያ መሆኑን የመቱ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
ሀገራዊ ምክክሩ ያሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ፣ የቆዩ አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለማስወገድና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ወሳኝ ነው።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በመቱ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ መምህርና ተመራማሪ በዳሳ አምሳሉ እንደተናገሩት ምክክሩ የጋራ ሀገራዊ ትርክትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ዘላቂ መፍትሔን ለመሻት ዓይነተኛ መሣሪያ ነው።
ሀገራዊ ፍላጎትና ጥቅምን ያስቀደመ ቋሚ አጀንዳ ለማንገብና ለተፈጻሚነቱ በጋራ ለመረባረብ ሁሉንም የማነሳሳት አቅም እንዳለውም አስረድተዋል።
ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ሂደቶች በንቃት በመሳተፍ ለሰላም ግንባታ ይበጃል ያለውን ሃሳብ በባለቤትነት ስሜት ማበርከት እንዳለበትም መክረዋል።
ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩት መምህር ሳቢት ዜይኑ በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ ለጋራ ሀገራዊ ትርክት ግንባታ የሚበጅ አዲስ እሳቤና ጠቃሚ እሴትን ያመጣል ብለዋል።
በዓለም ላይ በምጣኔ ሀብት ያደጉና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሀገራት መሰረታቸውን በወል ትርክት ላይ በመገንባትና ለሀገራዊ ጥቅምና ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት መሆኑንም ተናግረዋል።
በምክከሩ ጠንካራ የወል ትርክትን በመገንባቱ ሂደት ሁሉም ዜጋ የራሱን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አስገንዝበው ከዚህም ተጠቃሚ የሚሆነው ህዝቡ ራሱ መሆኑን አብራርተዋል።
በወል ትርክት የተገነባ ሀገር በትናንሽ ችግሮች እንዳይበገር ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት መምህሩ፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ቀዳሚ እንድትሆን በወል ትርክት ላይ የምትሰራው ስራ ትልቅ ሚና እንዳለውም አውስተዋል።