ቀጥታ፡

ወለጋ ወደ ሌላ የልማት ምዕራፍ ተሸጋግሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2018(ኢዜአ)፦ በወለጋ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች ወለጋ ወደ ልማት ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያሳዩ ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖች ያደረጉትን የስራ ጉብኝት በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአስተያየታቸውም የሰላም እጦት እና የግጭት ቀጣና መገለጫ ተደርጎ ይታይ የነበረው ወለጋ እና አካባቢው ወደተትረፈረፈ ልማት መሸጋገሩን ገልጸዋል።

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸው የቡሳ ጎኖፋ ኦሮሚያ የተቀናጀ የምግብ ኢንዱስትሪ ግንባታ መጀመሩ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

የተቀናጀ የምግብ ኢንዱስትሪ ግንባታው ለግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፍ እድገት አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ምንዛሬ ታወጣበት የነበረው በሀገር ውስጥ አቅም መተካት የሚያስችል ፕሮጀክት መጎብኘቱንም ነው የተናገሩት።

በዓመት ከ700 እስከ 800 ሚሊየን ዶላር ገቢ ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት ፕሮጀክት ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ በማህበር በመደራጀት ፋብሪካ ማቋቋምን ጨምሮ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ወለጋ ወደ ሌላ የልማት ምዕራፍ ተሸጋግሯል ያሉት ዶክተር እዮብ ይህም የሀሳብ ልዕልና እና የአላማ ጽናትን የሚያሳይ ነው ብለዋል።


 

የለውጡ መንግስት በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ የኢትዮጵያን የልማት አቅም አውጥቶ መጠቀምን የትኩረት አጀንዳ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝና የወለጋ ልማትም የዚሁ መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ነቀምት እንዳላት የልማት አቅም እስከ አሁን ሳይሰራ መቆየቱን አውስተው ህዝብ እና መንግስት ባከናወኑት የጋራ ስራ በከተማዋ ከሚጠበቀው በላይ ትርጉም ያለው ለውጥ መታየቱን አመልክተዋል።

አሁን የልማት እና የብልጽግና ዘመን ነው ያሉት ዶክተር እዮብ ሁሉም ለልማት እና እድገት እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም