ቀጥታ፡

የቡና ምርታማነትና ጥራትን ለማሳደግ ለክህሎት ልማት ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የቡና ምርታማነትን እና ጥራትን ለማሳደግ ለባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች ክህሎት ልማት ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።


 

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የቡና ጥራትን በመጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የክህሎት ስልጠናዎች ሚና ወሳኝ ነው። 

በዚህም የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ኢንተርፕራይዞች ድረስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ ቅንጅታዊ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ጋር የተደረገው ስምምነት የዚህ ጥረት አካል መሆኑን ተናግረዋል። 

ስምምነቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እስከ አርሶ አደሩ ለማድረስ የሚያስችል እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የባለሙያዎችን የመፈጸም አቅም በመገንባት ምርታማነት እና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ኢንስቲትዩቱ ከቡና ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን በማሻሻል ረገድ ትርጉም ያለው ስራ እንዲሰራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።


 

በተጨማሪም ቡና ላይ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚሰሩ አመልክተው፤ ንግድን ታሳቢ ያደረጉ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም