አርበኞች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተቀዳጁትን ድል የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ መድገም ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
አርበኞች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተቀዳጁትን ድል የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ መድገም ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-ቀደምት አርበኞች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር የተቀዳጁትን ድል የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና በማረጋገጥ መድገም እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ ገለጸ።
የካቲት-12 የሰማዕታት 89ኛ የመታሰቢያ ቀን እናትና አባት አርበኞችን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሃውልት ተከብሯል።
ለኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነት መስዋዕትነት ለከፈሉ እናትና አባት አርበኛ ጀግኖች ስድስት ኪሎ በሚገኘው የሰማዕታት ሃውልት የአበባ ጉንጉን የማኖር ሥነ-ሥርዓትም ተካሂደል።
የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ የባህል ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አዲሱ ሻንቆ፤ ጀግኖች አርበኞች ለሀገራቸው በከፈሉት መስዋዕትነት የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ አስረክበዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት ለማስከበር ጀብዱ የፈጸሙ ቀደምት አርበኞችን ማሰብም ለሀገር ክብር የሚቆም ተተኪ ጀግና ለማፍራት ትልቅ ስፋራ የሚሰጠው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም ቅድመ አያቶች በዓድዋ ተራሮች በወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጁትን ድል ለመዘከርም በመሃል አዲስ አበባ የዓድዋ መታሰቢያ ተገንብቶ ለህዝብ ክፍት መደረጉን አስረድተዋል።
የአሁኑ ትውልድም ቅድመ አያቶች ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊ አንድነት የከፈሉትን አኩሪ ገድል የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
ለዚህም ሀገራዊ አንድነትን በማጽናት በሁሉም የልማት መስክ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በበኩላቸው፤ የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና አንድነት በመጠበቅ የቅድመ አያቶችን የታሪክ አደራ መጠበቅ አለበት ብለዋል።
ቅድመ አያቶች ለኢትዮጵያ ክብርና ነፃነት የከፈሉት አኩሪ ተጋድሎም ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ትምህርት መሆኑን ገልጸዋል።
በየዓመቱ የሚከበረው የሰማዕታት ቀንም ቀደምት አርበኞች ለሀገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት ትውልድ እንዲዘክረው ለማስቻል የማይተካ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባል ደጀኔ ጨብሰታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቅድመ አያቶች ለሀገራቸው የከፈሉት ከፍተኛ ተጋድሎ የሀገር ፍቅርን በተግባር ያረጋገጠ ነው።
በዚህም የአሁኑ ትውልድ ከቅድመ አያቶቹ የተረከባትን ሀገር ዕድገትና ብልጽግና በማፋጠን ገንቢ ሚና ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝብዋል።
ተተኪ አርበኛ ዋና ሳጅን ስዩም ኪዳኑ በበኩላቸው፤ የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን በማጽናት የቅድመ አያቶቹን የታሪክ አደራ ማክበር እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።