ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በወረርሽኝ መከላከልና በክትባት ሥራዎች ላይ ውጤታማ ተግባር አከናውናለች

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ በወረርሽኝ መከላከልና በክትባት ሥራዎች ላይ ውጤታማ ተግባር ማከናወኗን የዓለም አቀፉ የክትባት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር  ጅሮም ኪም ገለጹ።

የኢትዮጵያ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መዋቅር ለወረርሽኝ መከላከል ትልቅ ሚና እንዳለውም ተገልጿል።

‎‎የዓለም አቀፉ የክትባት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶክተር  ጅሮም ኪም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ  እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በወረርሽኝ መከላከልና በክትባት ሥራዎች ላይ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር እያጠናከረች ትገኛለች። 

‎ኢትዮጵያ በክትባት ምርምርና ለድንገተኛ ወረርሽኞች በሚደረጉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ላይ በስፋት እየተሳተፈች መሆኑንም ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

‎በተለይም የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በኮሌራ ክትባት ሥራዎች ላይ ያከናወኑት ተግባር የኢትዮጵያን ውጤታማ የጤና ፖሊሲ ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት የቀጣናው የክትባት ቡድን መሪ ፕሮፌሰር ኤለን ሪስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ማንኛውንም የጤና ስጋት አስቀድሞ ለመከታተልና ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ የጤና ሥርዓት መዘርጋቷን ገልጸዋል። 


 

በተለይም እስከ ታችኛው የገጠር ቀበሌዎች ድረስ የተዘረጋው የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አዳዲስ ወረርሽኞችን ገና በጅምራቸው ለመለየትና ለመቆጣጠር ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

‎‎ለዚህም የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና የማህበረሰብ አቀፍ መዋቅሮች እንደ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ በማገልገል፣ በበሽታ መከላከል ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።

‎አሁን ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ይህንኑ የማህበረሰብ አቀፍ ጥንካሬ መነሻ በማድረግ፣ የክትባት ምርምር ሳይንስንና የማምረት አቅምን ለማሳደግ በከፍተኛ ፍላጎት እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል። 

‎‎መንግስት ያሉትን አማራጮች በመለየትና ስጋቶችን በአግባቡ በመምራት ረገድ እያሳየ ያለው ብቃት ለቀጣናው አርአያ ሊሆን እንደሚችልም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የማህበረሰብ አቀፍ ጥንካሬን መነሻ በማድረግ የክትባት ምርምርና የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ በከፍተኛ ፍላጎት እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል። 

መንግሥት አማራጮችን እና የጤና ስጋቶችን አስቀድሞ በመለየት ረገድ እያሳየ ያለው ብቃት ለቀጣናው አርአያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም