ቀጥታ፡

የጸጥታ ስጋቶችን አስቀድሞ መከላከልና እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅም ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የጸጥታ ስጋቶችን አስቀድሞ መከላከልና እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ አቅም መፈጠሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ሁለተኛው የጣሊያን አፍሪካ ስብሰባ የፀጥታ ዕቅድ አፈፃፀም የማጠቃለያ ግምገማ መርሀ ግብር አካሂዷል።

በአዲስ አበባ ከየካቲት 4 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት ሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ፣ 39ኛው የመሪዎች ጉባኤ፣ የጣሊያን አፍሪካ ስብሰባ፣ እና የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን የኢትዮጵያ ጉብኝት መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል፡፡

በእነዚህ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከ20ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡




የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በብቁ የሰው ሀይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና ደህብነት ስራ እየተከናወነ ነው።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በጠንካራ ተቋማዊ ቅንጅትና መናበብ አዲስ አበባ ያስተናገደቻቸው ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስችሏል ብለዋል፡፡

በተቋማትና ስምሪት በወሰዱ አባላት መካከል በተግባር የተፈተነ መልካም ትብብርና ቅንጅት በመፍጠር የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ፣ የጣሊያን አፍሪካ ስብሰባና የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት በስኬት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና መሰል የልማት ስራዎች ለተማዋ የጸጥታ ስራ ገንቢ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የሰው ኃይል አቅሙን በማሳደግ አደጋን አስቀድሞ መከላከልና ሲከሰትም በፍጥነት ርምጃ መውሰድ የሚያስችል አቅም መገንባቱን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያስተናገደቻቸው ዓለም አቀፋዊና አሕጉራዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ በቂ ዝግጅት መደረጉን በማስታወስ፤ የጸጥታና ደህንነት ስራዎች ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች እንዲታገዙ ተደርገዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተለዩ የቴክኖሎጂ አቅሞችን መታጠቁን ገልጸው፤ የሲ.ሲ.ቲቪ ካሜራዎችና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች እንዲገቡ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዘመናዊ ሞተር ሳይክሎችና ተሽከርካሪዎችን በማስገባት የሎጂስቲክስ አቅማችንን በከፍተኛ ደረጃ አሳድገናል ነው ያሉት፡፡

በመላ ኢትዮጵያ ጸረ ሰላም እንቅስቃሴዎችን አስቀድሞ ማስቀረት የሚያስችል የመረጃ ማሰባሰብና ስምሪት መደረጉንም ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ መርምራ የሚካሄድበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ አካባቢውን በመጠበቅና ለጸጥታ ኃይሉ መረጃ በመስጠት የጎላ አበርክቶ እያደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በሁነቶቹ የተገኘው የፀጥታ ስራ ስኬት ኢትዮጵያ በቀጣይ የሚካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በስኬት ለማከናውን ልምድ የተቀሰመባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም