ሴቶች ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ስኬት ሚናቸውን በበለጠ እንዲወጡ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ስኬት ሚናቸውን በበለጠ እንዲወጡ ተመለከተ
ደሴ፤ የካቲት 12/2018(ኢዜአ)፦ ሴቶች በዘላቂ ሰላም ግንባታና በልማት ስራዎች ተሳትፏቸውን በማጠናከር ለሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞ ሰኬት ሚናቸውን በበለጠ እንዲወጡ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሀዲ አመለከቱ።
"በሴቶች ተሳትፎ የፀናች እና የበለፀገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በደሴ ከተማ የውይይት መድረከ ተካሂዷል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ በሚካሄዱ የዘላቂ ሰላም ግንባታ እንዲሁም በልማትና በዲሞክራሲ ስራዎች የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገበውን የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ መትጋት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሴቶች ለማህበረሰቡ ያላቸውን ቅርበት ተጠቅመው ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ማማ ለማሸጋገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት ሚናቸውን በበለጠ መወጣት እንዳለባቸው አመልክዋል።
በተለይም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አበክረው እንዲሰሩ አስገንዘበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ሴቶች ክንፍ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ኢሌኒ አባይ በበኩላቸው፣ በሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ የበለጸገችና የጸናች ሀገር ለመፍጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን ጥቃትና ሁለተናዊ ችግር በማቃለል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የመሳተፍ አቅማቸውን ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል።
የተጀመረውን መልካም ተግባር ዳር ለማድረስ በበለጠ ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል ።
በደሴ ከተማ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ ነው ያሉት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አዝመራ ማስረሻ ናቸው።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሀዊና አሳታፊነት በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ከወዲሁ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጥሩዬ ሰይድ እና ወይዘሮ መሰረት ታደሰ በሰላምና በልማት ስራዎች ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።
በመድረኩ ለይ የፌዴራል፣ የክልል፣ የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።