ዩኒቨርሲቲው ህገ-ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ማዕከል አቋቁሟል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው ህገ-ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የወጣቶች የሥራ ፈጠራ ማዕከል አቋቁሟል
ጎንደር ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ህገ-ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል የሚያስችል ወጣቶች የሥራ ፈጠራ ሀሳባቸውን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ማዕከል ማቋቋሙን አስታወቀ።
ዩኒቨርሲቲው በህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ፍልሰት ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በጎንደር ከተማ አካሄዷል።
በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ክብሮም አድኖ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በአለም ላይ 70 በመቶ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚካሄደው በደላሎች አማካኝነት ነው።
ህገ-ወጥ የሰዎች ፍልሰት ሞት፣ የአካል ጉዳት ብሎም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያስከትል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ድርጊት ለመከላከልም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የችግሩን አሳሳቢነት በጥናትና ምርምር ስራዎች ከማሳየት ባለፈ የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ የሥራ ፈጠራ ማዕከል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ማዕከሉ ወጣቶች ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው በሀገራቸው ሰርተው የሚለወጡበትን የኢኮኖሚ አውድ እያመቻቸ መሆኑንም አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ አዲሱ ገድሉ (ዶ/ር) በአለም ከጦር መሳሪያና ከአደንዛዥ እፅ ቀጥሎ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚንቀሳቀስበት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መሆኑን ገልጸዋል።
ስር የሰደደ ድህነት፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች እንዲሁም ሥራ አጥነት ለህገ-ወጥ ፍልሰቱ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሕጋዊ የውጪ ሀገር የሥራ ስምሪትን ጨምሮ በአገር ውስጥ የስራ ዕድልን ለማስፋት አበረታች እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፍትህ መምሪያ ኃላፊ ግርማ ጌታቸው ፤ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በብሔራዊ የትብብር ጥምረት 16 ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።