በክልሉ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በሪፎርሙ በተሰሩ ሥራዎች የሚታዩ ውጤቶች ተገኝተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የፍርድ ቤቶችን አሰራር ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በሪፎርሙ በተሰሩ ሥራዎች የሚታዩ ውጤቶች ተገኝተዋል
ባህር ዳር፤ የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የፍርድ ቤቶችን አሰራር ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ በሪፎርሙ በተሰሩ ሥራዎች የሚታዩ ውጤቶች መገኘታቸውን የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በባህርዳር ከተማ ለሚያስገነባው የዳኝነት ኮምፕሌክስ ህንፃ ከኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የማማከር ውል ሥምምነት ተፈራርሟል።
የፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንት ዓለምአንተ አግደው በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፣ ከፍትህ ሥርዓቱ የሪፎርም ተግባራት አንዱ ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር ነው።
የፍርድ ቤቶችን አሰራር ቀልጣፋና ተደራሽ ለማድረግ እስካሁን በሪፎርሙ በተሰሩ ሥራዎች የሚታዩ ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶችን በቴክኖሎጂ በማስታጠቅ ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንና በዚህም የሕብረተሰቡ እንግልት መቀነሱን አንስተዋል።
ተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን በማስቀረትና ባለጉዳዩ ካለበት ሆኖ አቤቱታ ማቅረብ እንዲሁም ፋይል መክፈት የሚችልበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑንም አመልክተዋል።
በክልሉ ስማርት ፍርድ ቤቶችን የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ፍርድ ቤቶችን የማዘመኑን ሥራ የበለጠ ለማጠናከር በአባይ ወንዝ ዳር በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ህንፃ እንደሚገነባ ተናግረዋል።
ግንባታው በጥራትና በቅልጥፍና እንዲከናወን የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የማማከር ሥራውን እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አንዋር ካሳሁን በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚያስገነባው ህንጻ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ኮርፖሬሽኑ የማማከር ሥራውን በአግባቡ ይወጣል ብለዋል።