የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲን በሰው ሃይልና ግብዓት ለማሟላት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲን በሰው ሃይልና ግብዓት ለማሟላት አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲን በሰው ሃይልና ግብዓት ለማሟላት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ2018 የግማሽ ዓመት የመንግስት የስራ አፈፃጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዓለማችን 2ኛው የኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲም ለመጪዉ ትዉልድ ምቹ የቴክኖሎጂ ምህዳር በመፍጠር ለዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬት አስቻይ ሁኔታን እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታላይዜሽን መሠረተ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወንደሰን ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ክህሎት ልማት ላይ አመርቂ ውጤት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የኢትዮጵያን የዲጂታል ልማት ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ተወዳዳሪ የሰው ሃብት በማፍራት፣ ጥናትና ምርምር የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም የወሰዱት ተነሳሽነትም መጪውን ጊዜ ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረትም ሁሉም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና እንዲወጡ አቅጣጫ መሰጠቱን አብራርተዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም በሰው ሃብት ልማትና ግብዓት የማሟላት ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የመጪው ዘመን የኢትዮጵያና የዓለም ተስፋ ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይም ብቁ ጥናትና ምርምር እንዲሁም የሰው ሃይል ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ እንደሚገኝ አንስተዋል።
ይህኑ ታሳቢ በማድረግ ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጂ የተካኑ ምሁራንን በማዘጋጀት በጥናትና ምርምር ዘርፍ ውጤታማ ምኅዳር እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።