ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካዊያን የመቻል ምሳሌ ድንቅ አህጉራዊ የልማት ስኬት ነው 

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካዊያን የመቻል ምሳሌ ድንቅ አህጉራዊ የልማት ስኬት መሆኑን ከናይጄሪያ የገንዘብ ሚኒስትር  የመጡ ከፍተኛ ባለሞያ ኦግቦናያ ኦኩቲ (ዶ/ር) ገለጹ።   

ዕውቁ የምጣኔ ሃብትና የፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያ እንዲሁም ከናይጄሪያ ገንዘብ ሚኒስትር የመጡ ከፍተኛ ባለሞያ ኦግቦናያ ኦኩቲ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለአፍሪካዊያን የመቻል ምሳሌ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው አቅም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በማሳካት የወሰዱት ቁርጠኝነትም ታሪክ የማይዘነጋው የአፍሪካዊያን ሕያው ትዕምርት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የነበረው የኢትዮጵያዊያን ንቁ ተሳትፎም አስደማሚና አፍሪካዊያን በራሳቸው አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በሚያደርጉት ጥረት በአርዓያነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በህዝብ ተነሳሽነት ያስመዘገበችው አንጸባራቂ የልማት ድልም የአፍሪካን የወደፊት አዲስ የልማትና የዕድገት ስትራቴጂ የቀየሰ መሆኑን አንስተዋል።

የሕዳሴ ግድብ ስኬትም የህዝብና መንግስትን ጥብቅ የመተማመን ትስስር በተግባር የገለጠ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም የኢትዮጵያዊያንን አንድነት በማጉላት አፍሪካዊያን ከውጭ ብድርና እርዳታ ጥገኝነት በመላቀቅ ግዙፍ አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚችሉ በተግባር ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያዊያን የሕዳሴ ግድብ ስኬትም ለአህጉራዊ የልማት ግቦች ስኬታማነት በምሳሌነት የሚወሰድ ነው ብለዋል።

አህጉራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ትስስርን በማስፋት አጋርነትን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።


 

በቀጣይም የአፍሪካ ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስርን በማጠናከር አህጉራዊ የልማት አጀንዳዎችን ለማሳካት በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።

የአፍሪካ የውሃ ሃብትና የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓትን በማሻሻል የሀገር ውስጥ፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ የልማት ዘላቂነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሕዳሴ ግድብ ቀጣናዊ የኃይል ትስስርን በመፍጠር የአፍሪካዊያንን የልማት መሻት የሚያሳካ በጋራ የመቆም ምሳሌ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም