ለጠቅላላ ምርጫው ከ500 በላይ ታዛቢዎችን አሰማርተናል- የሲቪክ ማህበራት - ኢዜአ አማርኛ
ለጠቅላላ ምርጫው ከ500 በላይ ታዛቢዎችን አሰማርተናል- የሲቪክ ማህበራት
አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ500 በላይ የሚሆኑ የረጅም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎችን ማሰማራታቸውን የሲቪክ ማህበራት ገለጹ።
በኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
የመራጮች ምዝገባ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፤ የእጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ ከጥር1 ቀን ጀምሮ በዲጂታል ስርዓት እየተካሄደ ነው።
በዚህም 42 ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተናጠል፣ 15 ፓርቲዎች ደግሞ በሁለት ጥምረትና በአንድ ግንባር ለመፎካከር ዕጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁ ይታወሳል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹ የሲቪክ ማህበራት ሀላፊዎች እንደተናገሩት፤ ከምርጫ ቦርድ ጋር በጋራ በመሆን ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል።
ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሂደት የምርጫውን ሁኔታ በመታዘብ የሚሳተፋ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሰልጠን በአገር አቀፍ ደረጃ ማሰማራታቸውን ነው የገለጹት።
‘ህብረት ለምርጫ’ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ ሳህለሥላሴ አበበ እንደገለጹት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በታዛቢነት የሚሳተፉ 510 የረጅም ጊዜ የምርጫ ታዛቢዎች ተሰማርተዋል።
የምርጫ ታዛቢዎቹ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ሂደት የፖለቲካ ምህዳሩን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር፣ የምርጫ ቦርድ አስተዳደርና ዝግጅትና ሌሎች እንቅስቃሴዎች የሚመለከቱ መሆኑን አብራርተዋል።
በምርጫ መሳተፍ እድሜያቸው የደረሰ ሰዎች ሀላፊነትና መብት መሆኑን ጠቁመው፤ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ምርጫ ግንዛቤ የሚፈጥሩ የመራጮች ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም እስከ ምርጫው ወቅት ድረስ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
‘ረዲም ዘ ጀነሪሽን ‘ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር መላኩ ስብሀት፤ የምርጫ ፍትሃዊነት መገለጫ አንዱ አሳታፊነት በመሆኑ ወጣቶች በመራጭነትና በታዛቢነት በንቃት እንዲሳተፉ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ማህበራዊ ሚዲያዎችና የጥበብ ስራዎችን በመጠቀም የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጎልበት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። በምርጫ ታዛቢነት የሚሳተፉ ከ250 በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን ማዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ዳይሬክተር ገነት ስዩም፤ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የምርጫ ቦርድ፣ የግሉ ዘርፍ፣ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ምርጫው አካታች፣ ፍትሃዊና ነጻ እንዲሆን ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።