አርሂቡ ብሎ በመጣራት፤ አንድ ማእድ በመጋራት ፍቅርና አብሮነት የሚገለጥበት ጥልቅ እሴት - ኢዜአ አማርኛ
አርሂቡ ብሎ በመጣራት፤ አንድ ማእድ በመጋራት ፍቅርና አብሮነት የሚገለጥበት ጥልቅ እሴት
ደሴ፤ የካቲት 12/2018 (ኢዜአ) ፡-አርሂቡ ብሎ በመጣራት፤ አንድ ማእድ በመጋራት ፍቅርና አብሮነት የሚገለጥበት ጥልቅ እሴት
ከደሴ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ሐይቅ ከተማ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቿ ዕውቅናን አትርፋለች።
ሐይቅ ሄዶ ብርቱካን፣ ዘይቱን፣ መንደሪን እንዲሁም ጣፋጭ ሸንኮራ አገዳን ሳያጣጥም ብሎም ሳይሸክፍ ወደ መጣበት የሚመለስ እንግዳ እምበዛም ነው።
በከተማዋ ከዋሄሎ ሰፈር እስከ አስመራ በር የሚጣራው የዓሳ ጥብስ ሽታ ሆድን ያላውሳል።ሐይቅ ሄዶ ዓሳ ሳይቀምሱ መመለስ ዘበት ነው።
ኩልል ያለ የብርጭቆ ውሃ የሚመስለውን የሎጎ ሐይቅ ባህር እየቃኘ፣ ንፁህ አየር እየተነፈሰ፣ በአርቲና አሽኩቲው መአዛ መንፈሱን እያደሰ የዓሳ ቁርጥና ጥብስ መገባበዝ የፈለገ ደግሞ ከከተማዋ ወደ ቀኝ አቅጣጫ የደቂቃዎች የእግር ጉዞ ማድረግ ብቻ ነው የሚጠበቅበት።
የአምባሰሏ ንግስት ማሪቱ ለገሰ ''አመለኛው እግሬ መሄድ የለመደ፤ ሐይቅን ሲዞር ውሎ ውጫሌ ወረደ” እያለች የተቃኘችላት ሐይቅ ውበቷ ጥልቅ፤ ፍቅሯ ለብዙዎች ስንቅ ሆኖ ተመላልሰው እንዲጎበኟት ይገፋፋል።
የሐይቅ ፈርጥ የሆነው የሎጐ ሐይቅ የታሪክና የባህል እሴቶች የተሰናሰሉበት አስደናቂ ስፍራ ነው። የጥንታዊ ገዳማት መገኛ እንደመሆኑም በአማኞችና በጎብኝዎች የሚመረጥ ስፍራ ነው።
ከ908-918 ዓ.ም የሐይቅ እስጢፋኖስ አባ ኢየሱስ ሞአ ገዳም አባ ሰላማ በተባሉ የኃይማኖት አባት አማካኝነት መሰራቱን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
በከተማዋ መጠሪያ የተሰየመውና በግርማ ሞገስ የተንጣለለው የሎጎ ሐይቅ ለከተማዋ ተጨማሪ የውበት አክሊል ሲሆን በተለይም ንጋትና ምሽት ላይ በባሕሩ ላይ የሚያርፈው የፀሐይ ብርሃን ለአካበቢው ልዩ ገጽታን በመስጠት መንፈስን የሚያድስ ትርዒት ይፈጥራል።
በሐይቅና አካባቢው አርሂቡ ብሎ በመጣራት፤ አንድ ማእድ በመጋራት ጥልቅ እሴት የሚገለጥበት በተግባርም የሰዎች እውነተኛ ደግነት የሚታይበት መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ።
ይህቺ ጥንታዊና ታሪካዊ ከተማ ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በተጀመረው የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት ሌላ የክብር ካባን ተጎናጽፋ እንግዶቿን “አርሂቡ” እያለች ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተመርቆ ሥራ የጀመረውና በ13 ነጥብ 3 ሄክታር ላይ የተንጣለለው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በጽሞና አእምሮን የሚያሳርፉበትና የሚዝናኑበት ስፍራ ሆኗል።
ሪዞርቱ የሄሊኮፕተር ማረፊያ፣ ሰፊ የስብሰባ አዳራሽ እንዲሁም 67 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ለሐይቅ ከተማ ተጨማሪ ውበት አጎናጽፏታል።
ሐይቅን ከጥንት ማንነቷ እስከ ሪዞርቱ ግንባታ የተሰናሰነ ታሪኳን የሚያውቁ የከተማዋ ነዋሪዎች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የሐይቅ ከተማ ነዋሪው አቶ እንድሪስ ሰይድ፤ አካባቢው በተፈጥሮ ውበት የታደለ፣ ዘመናትን በዘለቀ የሰዎች ደግነትና አብሮነት መገለጫ ነው ይላሉ።
በማህበራዊና ሃይማኖታዊ ሁነቶች የማይለያየው የአካባቢው ነዋሪ ጣፋጩን የሐይቅ ዓሳ በአንድ ማእድ የሚጋራ፣ በደቦ የሚሰራ ተሳስቦና ተከባብሮ የሚኖር እንግዳውን “አርሂቡ” እያለ በፍቅር የሚቀበል መሆኑን ገልጸዋል።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መገንባት ተሸፍኖ የኖረውን የተፈጥሮ ውበት የገለጠ፣ እምቅ ታሪኳን ያጎላ ስለመሆኑ አንስተው፣ ሐይቅ ታላላቅ እንግዶቿን “አርሂቡ” በማለት በፍቅር ተቀብላ በሪዞርቷ አሳርፋ፣ ጣፋጭ ዓሳዋን ጋብዛ ለማስተናገድ ዝግጁ ሆናለች ብለዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አዲሴ እሸቱ ሐይቅና አካባቢው ያለውን እምቅ የተፈጥሮና የቱሪዝም ሃብት፣ ጠንካራ ማህበራዊ መስተጋብር የበለጠ ለመግለጽ የሎጎ ሪዞርት ቁልፍ ሚና አለው ይላሉ።
ለዘመናት ተዘንግቶ የነበረው የሎጎ ሐይቅና የከተማዋ መሰረተ ልማት የብዙዎች ቁጭት እንደነበር አስታውሰው፣ ሐይቁ ከእንክብካቤ ጉድለት የመጥፋት አደጋ ተጋርጦበት ነበር ብለዋል።
የሎጎ ሪዞርት ግንባታ ሐይቁን ከመጥፋት ከመታደግ ባለፈ ከከተማዋ የኮሪደር ልማት ጋር ተሰናስሎ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንዳደረጋትና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ያነሳሉ።
የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ከድር መሀመድ፤ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የተገነባው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ከተማዋን ከዘመናት ቁዘማ በማውጣት ልማትና ዕድገቷ እንዲፋጠን አድርጓል ይላሉ።
የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ግንባታ ከውበትና ሥራ እድል ፈጠራ ባለፈ የአካባቢውን መልክአ ምድርና ብዝሃ ሃብት መጠበቅ ያስቻለ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ሐይቁን ከመጥፋት አደጋ ከመታደግ ባለፈ ሐይቅ እስጢፋኖስን ጨምሮ ሌሎችም ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የቱሪዝም ሀብቶችን በማልማት የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነትና የከተማዋን የማደግ ተስፋ ያለመለመ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የአምባሰሏ ንግስት “ሐይቅን ሲዞር ውሎ ውጫሌ ወረደ” በማለት ያቀነቀነችላት ሐይቅ ከተማ አሁን ላይ ሐይቅን ሲዞር ለሚውል ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ምቹ ማረፊያ ሆኖ ተገኝቷል።