ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን አሳድገዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን አሳድገዋል
ሚዛን አማን፣የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፥ብልጽግና ፓርቲ ሁለንተናዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ባከናወናቸው ተግባራት የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማደጉን በፓርቲው የሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምነሽ ደመቀ ተናገሩ።
"በሴቶች ተሳትፎ የጸናችና የበለጸገች ኢትዮጵያ!" በሚል መሪ ሀሳብ የሴቶች የውይይት መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምነሽ ደመቀ እንዳሉት፥ በፓርቲው መሪነት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በፖለቲካ፣በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ የለውጥ እሳቤዎችና በተሰሩ ሥራዎች ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ጎልታ እንድትታይ ለማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በየዘርፉ በተከናወኑ ሥራዎች ውጤት መመዝገቡንና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትም እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሴቶች በአመራርነት እና በውሳኔ ሰጭነት ላይ ድርሻቸው ከፍ እንዲል የተደረገው ጥረት አበረታችና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑንም አንስተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በበኩላቸው፥ ሴቶች ለሀገር ሰላምና ዕድገት ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ሀገር የሚያሻግር ሀሳብ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፥ሴቶች በተለያየ ዘርፍ በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሳድጉ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥራ እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የድህነት ታሪክ እንዲቀይር የሚያስችሉ የልማት ተግባራትን በስፋት ማከናወኑን ጠቅሰዋል።
በዚህም ሂደትም ሴቶች በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች በመሳተፍ ተጠቃሚነታቸውን አሳድገዋል ብለዋል።
በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ ከቤንች ሸኮ ዞን ሁሉም መዋቅሮች የተወጣጡ ሴቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።