ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ሰፊ ትልሞች ለማሳካት በሁሉም ዘርፍ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው 

አሶሳ፤ የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ሰፊ ትልሞች ለማሳካት በሁሉም ዘርፍ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና የሶሺዮ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ሙሐመድ ኢብራሂም ተናገሩ።

39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውኃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ በተሳካ ሁኔታ  መካሄዱ ይታወቃል።

በጉባኤው ላይ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተነደፈውን አጀንዳ 2063 ለማሳካት የሚደረገው ጥረት በጥሩ ሂደት ላይ የሚገኝ መሆኑም ተነስቷል።

ለአጀንዳው ስኬት የአባል አገራቱ የመፈፀም አቅምና ቁርጠኝነት ወሳኝ በመሆኑ በዚሁ እሳቤ መስራት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ሚና እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?  በማለት ኢዜአ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና የሶሺዮ ኢኮኖሚ ተመራማሪ ሙሐመድ ኢብራሂምን አነጋግሯል።

የአፍሪካን መፃኢ ዕድል ለመወሰን የአገራት ትብብርና የጋራ ልማት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ምሁሩ የእያንዳንዱ አገር ጥረትም የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት ጥረት በቀጣናውም ይሁን በአህጉሩ የስኬት መንገድ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጭምሮ ሌሎች ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በማከናወን ከራሷ አልፎ ለአካባቢው አገራት የጋራ ልማትና ተጠቃሚነት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

በአህጉራዊ የሰላም ግንባታም ይሁን በግብርናው ዘርፍ በተለይም በስንዴ ምርት ከራሷ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ጭምር የመሪነት ሚናዋን እያሳየች ትገኛለች ብለዋል።

በመሆኑም ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ስኬት በሁሉም ዘርፎች የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እና ሚና ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም ለጎሮቤት አገራት ቅድሚያ በመስጠት በኃይል፣ በትራንስፖርት እና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ለማስተሳሰርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ጥረት ውስጥ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን የማስከበር እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኗን ያነሱት መምህሩ፤ የቀጣናው ብሎም አጠቃላይ የአፍሪካ አገራት ትብብርና ድጋፍ ሊደረግላት ይገባል ብለዋል።

አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት እንዲሁም የአፍሪካን መልካም ጥረቶች የሚያሳይ ትርክት በመገንባት ረገድ የኢትዮጵያ ጥረት በጉልህ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ አጀንዳ 2063 ዋና ዋና ትልሞች አህጉራዊ ብልጽግናን ማምጣት፣ የልማት ትስስር መፍጠር፣ ዘላቂ ሰላምና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም