ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ መተባበርና በጋራ መበልጸግ ላይ ያላትን ጽኑ አቋም ያረጋግጣል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 12/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ተግባራዊ የምታደርጋቸው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎች መተባበርና በጋራ መበልጸግ ላይ ያላትን ጽኑ አቋም የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየና የዳበረ የዲፕሎማሲ ባህል አላት። 

አሁንም ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶቿ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የተቃኙ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዘርፉ በርካታ ውጤቶች እንዲመዘገቡ እድል ፈጥሯል ብለዋል።

የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚደረግ በጋራ ማደግና መበልጸግ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም አንስተዋል።

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኤርትራ መንግስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የላከው ግልጽ ደብዳቤ ዲፕሎማሲያዊ አካሔድን የተከተለ መሆኑንም በአብነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ለሰላም እና ለትብብር ያላትን ጽኑ አቋም የሚያሳይና ቁርጠኝነቷን የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ደብዳቤው አሁናዊ ነባራዊ ሁኔታውን በግልጽ ያስቀመጠ እና ለችግሮች መፍትሔውን ጭምር ያመላከተ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ የትኛውንም ሁኔታ በንግግር ለመፍታት ስላላት ቁርጠኝነት ደብዳቤው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለዋል።

ይህም የኢትዮጵያ መንግስት አሁንም ለሰላም እድል እንደሚሰጥና አማራጩ ንግግርና ድርድር መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

እንዲሁም ኢትዮጵያ ሰላምና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ከራሷ አልፎ ለኤርትራ ህዝብና መንግስት ወሳኝ መሆኑንም ጭምር ያሳየ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅትም ትልቅ ሀገራዊ የመንግስትና የህዝብ አጀንዳ የሆነው የባህር በር ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ ድርድር ለማስፈጸም የምታከናውነው ተግባር አንዱ የዲፕሎማሲ መንገድ መሆኑንም ተመራማሪው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በየትኛውም መስክ እያስመዘገበች ያለው ስኬት ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷ እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸው፤ ይህም ለቀጣናው ሀገራት ምሳሌ ያደርጋታል ነው ያሉት።

የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ፕ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ሊኖራት እንደሚገባ የተያዘው ጠንካራ አቋም ተገቢና ለሀገርና ለህዝብ ህልውና መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችበት መንገድ ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው፤ ሀገሪቷ ችግሮችን ግልጽ፣ ሰላማዊና በድርድር ሒደት የመፍታት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

በመሆኑም ከኢትዮጵያ መንግስት የቀረበውን መተባበርና በጋራ መበልጸግ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ህዝብ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ጥያቄውን በአዎንታ መቀበል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለጥያቄው ስኬታማነት መንግስት የጀመራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ሒደቶች ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተመራማሪው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመሆኑም የመንግስትን ዲፕሎማሲያዊ ጥረትና ፍላጎት መደገፍና ለአፈጻጸሙ ስኬታማነት ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም