ቀጥታ፡

ነፋሻማው የጎዴ ፓርክ በወጣቶች ተመራጭ የመዝናኛ ሥፍራ ሆኗል

ጎዴ፤ የካቲት 12/2018 (ኢዜአ) ፡-ነፋሻማው የጎዴ ፓርክ በወጣቶች ተመራጭ የመዝናኛ ሥፍራ ሆኗል።

በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።

የከተማዋን ውበት የሚገልጡና የክልሉን እድገት የሚያፋጥኑ የወጣቶች መዝናኛና መናፈሻ ስፍራዎች መገንባታቸው ደግሞ የአካባቢውን ገጽታ ከመቀየር አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

በሞቃታማዋ ጎዴ ከተማ የተገነባው የክፍለ ዘመን መዝናኛ ፓርክ የዚሁ አካል ሲሆን በፓርኩ የሚገኙ እጽዋት አካባቢውን ነፋሻማ በማድረግ ለወጣቶች አማራጭና ተመራጭ መዝናኛ ሥፍራ ሆኗል።


 

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ወጣቶች ፓርኩ ውብና አረንጓዴ በመሆኑ ሞቃታማውን የአካበቢውን አየር ጸባይ ነፋሻማና ምቹ አድርጎታል ይላሉ።

የከተማዋ ወጣቶች ለመዝናናትም ሆነ ለንባብ የሚመርጡት ቦታ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወጣት ሀምዛ አብዱልዋሃብ እንደሚለው ፓርኩ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአልባሌ ስፍራ እንዳያሳልፉ አማራጭ መዝናኛ ሆኗል።

ወደ ፓርኩ በተደጋጋሚ በመምጣት አንደሚያነብና እንደሚዝናናም ገልጿል።

ለተለያዩ ዝግጅቶች ፓርኩን ተመራጭ መዳረሻ እንደሚያደርግ የገለጸው ደግሞ ወጣት ሳዳም ሁሴን ነው።

ፓርኩ ከአካባቢው ወጣቶች ባለፈ ወደ ጎዴ ለሚመጡ እንግዶች ተመራጭ የመዝናኛ ቦታ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣት ዴቃ መሀመድ በበኩሏ የፓርኩ መገንባት ውብና አረንጓዴ አካባቢ በመፍጠር በነፋሻማ አየር  ጊዜዋን አንድታሳልፍ ዕድል መፍጠሩን ገልጻለች።


 

የጎዴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አሊ፣ ከተማዋን አረንጓዴና ዉብ የማድረግ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ፓርኩ ለወጣቶች አማራጭ የመዝናኛ ቦታ ከመሆን ባለፈ ለአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም