ቀጥታ፡

የፀጥታና ደህንነት ግብረ ኃይል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በስኬት እንዲስተናገዱ በማድረግ የኢትዮጵያን አቅም በተግባር አስመስክሯል-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የፀጥታና ደህንነት ግብረ ኃይል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በስኬት እንዲስተናገዱ በማድረግ የኢትዮጵያን አቅም በተግባር ማስመስከሩን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ሁለተኛው የጣሊያን አፍሪካ ስብሰባ የፀጥታ ዕቅድ አፈፃፀም የማጠቃለያ ግምገማ መርሀ ግብር አካሂዷል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የፀጥታና ድህነት ስራ በብቁ የሰው ሀይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ነው።

የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሀይል ከየካቲት 4 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄዱ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን ዘመቻና የፀጥታ ስምሪት ማድረጉን ገልጸዋል።

በዚህም 48ኛው የአፍሪካ ሕብረት ሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ፣ 39ኛው የመሪዎች ጉባኤ፣ የጣሊያን አፍሪካ ስብሰባ፣ እና የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በኢትዮጵያ ጉብኝት በስኬት ተጠናቀዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሰው ሀይልና ቴክኖሎጂ ትጥቅ አቅሙን ከማሳደጉ በተጨማሪ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች ለፀጥታ ስራዎች ተጨማሪ አቅም መፍጠራቸውን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና አሕጉራዊ ሁነቶችን በስኬት ለማስተናገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ በቂ የሰው ሀይል ስምሪት ተደርጓል ብለዋል።

ተቋማትና ስምሪት በወሰዱ አካላት መካከል በተግባር የተፈተነ መልካም ትብብርና ቅንጅት በመፈጠሩ የተገኘ ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

በሁነቶች የተገኘው የፀጥታ ስራ ስኬት ኢትዮጵያ በቀጣይ የሚካሄደውን 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፣ የኮፕ 32 እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ሁነቶችን በስኬት ለማከናውን ልምድ የተቀሰመባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም