ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶች የግብርና ምርታማነትን በማፋጠን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፤የካቲት 12/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶች የግብርና ምርታማነትን በማፋጠን የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እመርታዊ ውጤት እያስገኙ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የመሬት ሃብት ያላት ሀገር ናት።

በሰብልና የእንስሳት ሃብት ምርታማነት አቅም የሆኑ ምቹ ከባቢያዊ የሥነ-ምኅዳርና የመሬት ሃብት የተጎናጸፈች መሆኗን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን የመሬትና የውሃ ሃብት ልማት በማጣጣም የግብርና ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የገጽ-ምድርና ከርሰ-ምድር የውሃ ሃብቶችም የኢትዮጵያን የግብርና ምርታማነት በማሳለጥ ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥም የግብርና እና ገጠር ፖሊሲ፣ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተቀረጸው የ10 ዓመት መሪ ዕቅድና የአስፈፃሚ ተቋማት መኖራቸውን አብራርተዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የግብርናውን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የሚያፋጥኑ አሰራሮች መተግበራቸው በሰብልና የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ላይ እመርታዊ ውጤት ማስገኘቱን አንስተዋል።

በግብርና ምርታማነት የተገኙ እመርታዊ ውጤቶችም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሂደትና በጥቅል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንዲይዝ ማስቻሉን ገልጸዋል።

የገንዘብ ተቋማት ለአርሶ አደሮች የሚያቀርቡት የግብርና ማሻሻያ የገንዘብ ብድር አገልግሎት ለዘርፉ ዕድገት ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም የአርሶና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም የግብርና ምርት እሴት ሰንሰለት ተዋናዮችን የማምረት አቅም በማሳደግ ተጠቃሚነትን እያሻሻለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የውሃ ሃብቶችም የአርሶና የአርብቶ አደሮችን ተለምዷዊ የግብርና አመራረት ባህል በመቀየር በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት የሚችሉበትን ዕድል ፈጥረዋል ብለዋል።

የውሃ ሃብትን በዘመናዊ መስኖ የማልማት ባህልም የግብርና ትራንስፎርሜሽን በማፋጠን የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም